በህዳሴው ግድብ ጉዳይ ግብጻውያን ሊታገሱ እንደሚገባ ፕሬዝዳንት አል ሲሲ ተናገሩ
ይህን ያሉት የስዊዝ ቦይ አካል የሆኑ የተለያዩ ፕሮጄክቶችን ባስመረቁበት በዛሬው ዕለት
ፕሬዝዳንቱ ስጋቱ ተገቢ ቢሆንም ድርድር ጊዜ የሚፈልግ ጉዳይ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል ብለዋል
የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ ግብጻውያን ሊታገሱ እንደሚገባ ተናገሩ፡፡
ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት የስዊዝ ቦይ አካል የሆኑ የተለያዩ ፕሮጄክቶችን ባስመረቁበት በዛሬው ዕለት ነው፡፡
በግድቡ ጉዳይ “መስጋታችሁ ተገቢ ነው” ሲሉ ለግብጻውያን መልዕክት ያስተላለፉት አል ሲሲ “ነገር ግን ልትታገሱ ይገባል” ብለዋል፤ ድርድር ጊዜ የሚፈልግ ጉዳይ መሆኑ ልብ ሊባል እንደሚገባ በመጠቆም፡፡
“መጣደፍ” እንደማያስፈልግ በማከልም “በሃገራችሁ በመሪዎቻችሁም ጭምር ልትተማመኑ ይገባል” ሲሉ በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡
የግድቡ ድርድር ጉዳይ “ጊዜ፣ትዕግስት እና ጥንቃቄ”ን የሚፈልግ ነው ብለዋል አል ሲሲ፡፡
መስጋቱ ተቀባይነት ያለው ቢሆንም “ችላ የማይባሉ መብቶች አሉን” ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡
ከግድቡ ጋር በተያያዘ የተደረጉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን በማስታወስም እልባት ያገኛል የሚል ተስፋ እንደላቸው ገልጸዋል፡፡
ፕሬዝዳንት አል ሲሲ የስዊዝ ቦይ መተላለፊያ “ኤቨር ጊቭን” በተሰኘች እቃ ጫኝ መርከብ በተዘጋበት ጊዜ በአካባቢው ተገኝተው ባደረጉት ንግግር “ከግብጽ የውሃ ድርሻ ላይ ማንም አንዲትንም ጠብታ ሊነካ” እንደማይችል የሚያሳስብ ንግግር ማድረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡