124 የመንግስት መስሪያ ቤቶች 14.1 ቢሊዮን ብር በወቅቱ ያልተወራረደ ወይም ያልተሰበሰበ ተሰብሳቢ ሂሳብ አለባቸው ተባለ
ውዝፍ ወይም ተሰብሳቢ ሂሳብ ከተገኝባቸው የመንግስት ተቋማት የጤና ሚንስቴር በ6 ቢሊየን ብር ቀዳሚው ነው
92 የመንግስት መስሪያ ቤቶች ተመላሽ እንዲያደርጉ ከታዘዙት 443 ሚሊዮን ብር ዉስጥ 394.8 ሚሊዮን ብር ተመላሽ አላደረጉም
የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የ2015 በጀት ዓመት የፌደራል መንግስት መስሪያ ቤቶች የፋይናንስ ህጋዊነት ኦዲት እና የክዋኔ ኦዲት ሪፖርትን በዛሬው ዕለት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል፡፡
በሪፖርቱ በ124 መስሪያ ቤቶች በጠቅላላው ብር 14.1 ቢሊዮን በወቅቱ ያልተወራረደ ወይም ያልተሰበሰበ ተሰብሳቢ ሂሳብ መኖሩ በኦዲት ታውቋል።
ለውሎ አበል እና ለመጓጓዣ እንዲሁም ለግዥ የተሰጠ ክፍያ ሰራተኛው ስራውን አጠናቆ ከተመልሱ በኃላ በ7 ቀናት መወራረድ እንዳለበት መመሪያው ቢያዝም ተቋማቱ ገንዘቡን በወቅቱ ባለማወራረዳቸው ከፍተኛ ውዝፍ እንዳለባቸው ነው የተነገረው።
በዚህም ከፍተኛ ውዝፍ ተሰብሳቢ ሂሳብ ከተገኘባቸው ተቋማት መካከል
• ጤና_ሚኒስቴር 6 ቢሊዮን
• የመስኖ ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር 1.1 ቢሊዮን
• የትምህርት ሚኒስቴር 1 ቢሊዮን 12 ሚሊዮን
• በፌዴራል መንግስት የህንጻዎች ግንባታ ፕሮጀክት ጽ/ቤት 970.9 ሚሊዮን
• ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚኒሊየም የህክምና ኮሌጅ 756.3 ሚሊዮን
• የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ 433.5 ሚሊዮን
• የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት 286.8 ሚሊዮን
• የአደጋ ስራ አመራር ኮሚሽን 272.4 ሚሊዮን
• የመንግስት ግዥ አገልግሎት 265.2 ሚሊዮን
• የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን 250.7 ሚሊዮን
• የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር በ218.3 ሚሊዮን ብር ከፍተኛ ውዝፍ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በተያያዘም 92 የመንግስት መስሪያ ቤቶች ተመላሽ እንዲያደርጉ ከታዘዙት 443 ሚሊዮን ብር ዉስጥ 394.8 ሚሊዮን ብር ተመላሽ አለማድረጋቸውን ዋና አዲተር መሠረት ዳምጤ ሪፖርቱን በንባብ ባቀረቡበት ወቅት አስታውቀዋል፡፡
ከ443 ሚሊየን ብሩ መመለስ የተመለሰው 48.2 ሚሊዮን ብር ብቻ ሲሆን በሌላ በኩል ማስረጃ ካልቀረበበት ከ 5 ቢሊዮን በላይ ብር ዉስጥ 510 ሚሊዮን ገደማዉ ብቻ አሳማኝ ማስረጃ እንደቀረበበት ተናግረዋል፡፡
ሪፖርት አክሎም 30 የፌደራል መንግስት መስሪያ ቤቶች 16 ሚሊዮን 470ሺህ ብር ከደንብና መመሪያ ውጪ አላግባብ መክፈላቸውን አረጋግጧል፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር በ 2014 በጀት አመት በቀረበለት ሪፖርት መሰረት ተቀባይነት የሚያሳጣ አስተያየት ከተሰጠባቸዉ 19 የመንግስት መስሪያቤቶች እና የኦዲት አስተያየት ሊሰጠባቸዉ ባልቻሉ ስድስት ተቋማት ላይ የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰዱ የተገለጸ ሲሆን፤ ከነዚህ መካከል
በስድስት ዩኒቨርስቲዎች እና በሰባት የመንግስት መስሪያቤቶች ላይ የገንዘብ ቅጣት እና ከባድ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ መጻፉን ዋና ኦዲተሯ አመላክተዋል። በተጨማሪም ሶስት የዩኒቨርስቲ አመራሮችም ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ ማድረጉን ይፋ አድርገዋል።