ለመጀመሪያ ጊዜ ዜጎችን ለማስተማር ለፖለቲካ ፓርቲዎች የተመደበው በጀት ስጋትን ፈጠረ
41 ሚሊዮን ብር የተመደበላቸው ፓርቲዎች በመንግስት ጫና ምክንያትት በጀቱን መጠቀም ያዳግተናል አሉ
ለ2015 ዓመት ከተመደበው 106 ሚሊዮን ብር በጀት ብልጽግና 19 ሚሊዮን ብር ገደማ ተመደበለት
ለመጀመሪያ ጊዜ ዜጎችን ለማስተማር ለፖለቲካ ፓርቲዎች የተመደበው በጀት ስጋትን ፈጠረ፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ከመንግስት የተገኘን 106 ሚሊዮን ብር የበጀት ድጎማ ለፓርቲዎች አከፋፍሏል፡፡
64 ሚሊዮን ብር ለመደበኛ ወጪና 41 ሚሊዮን ብር ለሲቪክ ትምህርት የተመደበ ሲሆን፤ ክፍፍሉም ፓርቲዎች ተስማምተውበታል በተባለ ቀመር መከፋፈሉ ተነግሯል፡፡
መመዘኛው በዋናነት በሴቶችና አካል ጉዳተኞ ተሳትፎ ላይ የሚያተኩር ሲሆን፤ አራት ነጥብ አራት ሚሊዮን ሴት አባለላት፣ ስምንት ሴት አመራሮችና 129 ሽህ አካል ጉዳተኛ አባላት አሉኝ ያለው ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛውን 11 ነጥብ አራት ሚሊዮን ብር መደበኛ በጀት በመውሰድ ቀዳሚ ሆናል፡፡ ኢዜማና የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ በቅደም ተከተል ሁለት ነጥብ ሰባት ሚሊዮንና ሁለት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ብር በመውሰድ ይከተላሉ፡፡
ብልፅግናን ጨምሮ 26 ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያካሂዱ ምርጫ ቦርድ አሳሰበ
ለመጀመሪያ ጊዜ ለሰለጠነ ፖለቲካ ማስተማሪያ የሚሆን የሲቪክ ትምህርት የሚውል 41 ሚሊዮን ብር ተበጅቷል፡፡
በጀቱ በተመሳሳይ መመዘኛ መመደቡን የተናገሩት የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚዴቅሳ፤ አባላትን ለማስተማር፣ ለውይይቶችና አጠቃላይ ዜጎችን ስለሰለጠነ ፖለቲካ ለማስተማር የሚውል ነው ብለዋል።
ፓርቲዎቹ በበጀቱ አስፈላጊነት ላይ ጥያቄ ባያቀርቡም፤ በመንግስት ጫና ግን በጀቱን ስራ ላይ ለማዋል እንደሚቸገሩ ተናግረዋል፡፡
አባላትን ማዋከብ፣ ማሰር፣ ጽ/ቤቶችን መዝጋትና እንደ ልብ ተንቀሳቅሶ ለመስራት ያለው የሰላምና ደህንነት ሁኔታ ውይይቶችን ለማድረግና ስልጠና ለመስጠት አስቸጋሪ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለአባላትና ለዜጎች ትምህርት ለመስጠት የሚያስችል ከባቢ የለም ያሉት ፓርቲዎች፤ በዋናነት ህዝባዊ አዳራሾችንና መሰብሰቢያዎችን ያለማግኘትና የመንግስት ተጽዕኖን አንስተዋል፡፡
ፓርቲዎቹ የግለሰብ አዳራሽ መከራየት አልቻልንም። ይሳቀቃሉ፤ ይፈራሉ፡፡ የህዝብ አዳራሾችና ሀብቶች ለመንግስት ብቻ ናቸው፡፡ የመንግስት ጫናና የደህንነት ችግር ባለበት ሁኔታ እንዴት በጀቱ ተፈጻሚ ይሆናል? የሚል ጥያቄ አንስተዋል።
በቃል ኪዳን ሰነዱ የፈረመ ፓርቲ ነው ተጽዕኖ የሚያሳድረው፡፡ ከጠብመንጃ ባለፈ በሀገሪቱ በሰላም እንዴት ነው የምንነጋገረው? ህዝቡን እንዴት ነው የምናነቃው? አባላትን እንዴት ነው መሰብሰብ የምንችለው? በማግስቱ ይታሰራሉ፡፡ ከፍተኛ ስጋት አለ፡፡ በህይወት ላይ ቁማር ነው ሲሉ ፓርቲዎቹ ስጋታቸውን ተናግረዋል፡፡
ለሲቪክ ትምህርቶች የተመደበው በጀት ህዝባዊ መሰብሰቢያ ስፍራዎችን ለማግኘት ችግር ከሆነ ጥቅም ላይ ሊውል አይችልም ያሉት የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱከን ሚዴቅሳ፤ አዳራሾች፣ ስታዲዬሞች ለሁሉም ፓርቲ እኩል ማገልገል አለባቸው ብለዋል፡፡ ይህም እንዲሆን ለመንግስት ጥሪ ያቀረቡት ሰብሳቢዋ፤ ቦርዱ አስፈላጊውን እገዛ ያደርጋልም ብለዋል፡፡
ብልጽግና ፓርቲ መደበኛ በጀት 11 ነጥብ አራት ሚሊዮን ብር፤ ለሲቪክ ትምህርት ሰባት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር በድምሩ 18 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር ገደማ ደርሶታል፡፡
ለበጀቱ መዘግየት ፓርቲዎች ሰነዶቻቸውንና የኦዲት ሪፖርታቸውን በቶሎ አለማቅረብ በምክንያት ተነስቷል።
36 ክልል አቀፍ ፓርቲዎችና 14 ሀገር አቀፍ ፓርቲዎች ብቻ ናቸው በበጀቱ የተደለደሉት። ጥቂት የማይባሉ ፓርቲዎች የኦዲት ሪፖርት ባለማቅረብ፣ በብክነት፣ በምዝበራና ማስረጃ ባለማቅረብ በበጀቱ አልተካተቱም።
።