ከ2016 በጀት ጋር ሲነጻጸር 200 ቢሊዮን ብር ገደማ የሚበልጠው ረቂቅ በጀቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተልኳል
የሚንስትሮች ምክር ቤት በ34ኛ መደበኛ ስብሰባው የ2017 በጀት አመት የፌዴራል መንግስት ረቂቅ የበጀት አዋጅን አጽድቋል።
የ2017 ዓ.ም የፌደራል መንግስት በጀት የአስር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ አካል የሆነውን የ2016-2018 የልማትና ኢንቨስትመንት እቅድ ላይ የተቀመጡ ግቦችን እና የ2017-2021 የመካከለኛ ዘመን የማክሮ ኢኮኖሚና የፊስካል ማዕቀፍን ማስፈጸም እንዲቻል በሚያደርግ መልኩ መዘጋጀቱን አስታውቋል።
እንዲሁም የ2016 የፌደራል መንግስትን የፕሮግራም በጀት አፈጻጸም መነሻ በማድረግ፤ የመንግስት የፋይናንስ አቅም እና ተጠባቂ ገቢዎችን ታሳቢ በማድረግ እንዲሁም አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች የተሰጣቸውን ተልኮና ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስፈልጋቸውን ወጪ በመገምገም እንዲዘጋጅ መደረጉንም ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ያነኘው መረጃ ያመለክታል።
በዚሁ መሰረት ለፌዴራል መንግስት መደበኛ ወጪዎች ፣ ለካፒታል ወጪዎች ፣ ለክልሎች የሚሰጥ ድጋፍ፣ ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ድጋፍ እና ተጠባባቂ ወጪን ጨምሮ ወደ 1 ትሪሊየን የሚጠጋ በጀት ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡
ምክር ቤቱ በቀረበው በጀት ላይ ተወያይቶ 'ግብዓቶችን በማከል' ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል።
ሰኔ 30 የሚጠናቀቀው የ2016 ዓመት በጀት 801.65 ቢሊዮን ቢሊዮን ብር ነው።
በሌላ ዜና ምክር የሚኒስትሮች ምር ቤት በዛሬው መደበኛ ስብሰባው የአረንጓዴ አሻራ እና የተጎሳቆለ መሬት ማገገሚያ ልዩ ፈንድን ማቋቋሚያ እና አስተዳደሩን ለመወሰን ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተወያየ ቨኋ ምክር ቤቱም ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ውሳኔ አሳልፏል።
የሚኒስትሮች ምር ቤት የነዳጅ እና ኢነርጂ ባለስልጣን እና የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ተቋማት ለሚሰጧቸው ልዩ ልዩ አገልግሎቶች የሚከፈሉ የአገልግሎት ክፍያዎችን ለመወሰን በቀረቡ ረቂቅ ደንቦች ተወያይቷል።
ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቦቹ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው ከወጡበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውሉ ወስኗል።