ፖለቲካ
ተመድ የትግራይን ጉዳይ በአጀንዳነት ያንሳው እንጂ የሚፈታው በኢትዮጵያ አመራር ነው-ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግድቡን በተመለከተ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበርን “እየጠበቅን ነው” ብሏል
የኢትዮጵያ መንግስት የቱኒዚያ አካሄድ በአፍረካ ህብረት እየተካሄደ ያለውን የድርድር ጥረት የሚያደናቅፍ መሆኑን ገልጿል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት በትግራይ ክልል ጉዳይ ስብሰባ እንደሚያደርግ ቢገልጽም፤ ጉዳዩ የሚፈታው በኢትዮጵያ መንግስት አመራር መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ መንግስት አጀንዳውን ተመድ ለምን አነሳው እንደማይል ገልጸው ጉዳዩ ግን የውስጥ በመሆኑ የሚፈታው በኢትዮጵያ አመራር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ይህንን አጀንዳ ለምን አነሱ የሚል ጥያቄ ውስጥ እንደማይገባ አንስተዋል፡፡ አሁን ላይ ስብሰባው ሳይደረግ በጉዳዩ ላይ አስተያየት መስጠት አስቸጋሪ እንደሆነም ነው አምባሳደር ዲና ሙፍቱ ተናግረዋል፡፡ በተለያየ መንገድ ማለትም በግድቡም፣ በህወሓት፣ በአግዋም፣ በዓለም ባንክ እና በዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም ብድር እንከለከላለን ቢባልም በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ግን ላይ መንግስት መቸም ቢሆን እንደማይደራደር ቃል አቀባዩ ገልጸዋል፡፡
በፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት በአፍሪካ ኮታ ተለዋጭ አባል የሆነችው ቱኒዚያ ለግብጽ ተገቢ ያልሆነ ድጋፍ ለማድረግ ያቀረበችው የውሳኔ ሃሳብ ውድቅ ቢደረግባትም በድጋሚ ለማቅረብ ዝግጅት ማድረጓንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከናይል የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት አምባሳደሮች ጋር ባደረጉት ውይይት ቱኒዚያ ያቀረበችው የውሳኔ ሃሳብ ቢወሰን የሁሉም የላኛው ተፋሰስ ሀገራት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሊያስገባ እንደሚችል መግለጻቸውን አምባሳደር ዲና ገልጸዋል፡፡
ይህንን የቱኒዚያን የውሳኔ ሃሳብ ለመቀልበስ በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ አምባሳደር ሬድዋን መግለጻቸውን አምባሳደር ዲና ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው፤ የቱኒዚያ አካሄድ በአፍሪካ ህብረት አስተባባሪነት እየተካሄደ ያለውን የሶስትዮሽ ድርድር ጥረት የሚያደናቅፍ መሆኑን መግላቸውን እና ሀገራቱ ኒውዮርክ ለሚገኙት ሚሲዮኖቻቸው ይህንኑ እንዲገልጹላቸው መጠየቃቸውን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡
የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ አሁን ላይ ኢትዮጵያ የወቅቱን የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር የስብሰባ ጥሪ እየተጠባበቀች እንደሆነም ተገልጿል፡፡