በአብዬ ግዛት የተሰማራው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦር እንዲወጣ ያቀረበችውን ጥያቄ ተመድ እንደተቀበላት ሱዳን አስታወቀች
ኢትዮጵያ ጦሬ ከአብዬ መውጣት ካለበትም ተገቢው ክብር ተሰጥቶት ነው ስትል ማስታወቋ የሚታወስ ነው
ሱዳን በአብዬ ግዛት የተሰማራው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦር ይውጣልኝ የሚል ጥያቄ ስታቀርብ ቆይታለች
በአብዬ ግዛት የተሰማራው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦር እንዲወጣ ያቀረበችውን ጥያቄ ተመድ እንደተቀበላት ሱዳን አስታወቀች፡፡
የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መርያም አል ሳዲቅ አል መህዲ ከተመድ ዋና ጸሃፊ የምስራቅ አፍሪካ ልዩ መልዕክተኛ ፓርፊት አንያንጋ ጋር ትናንት ሰኞ ምሽት የበይነ መረብ ውይይት አድርገዋል፡፡
በውይይቱ የድርጅቱ የሰላም አስከባሪ ዋና ኃላፊ ዦን ፔሬ ላክሮይ እንዲሁም የኦፕሬሽን ዋና ኃላፊ አቱል ካሪ ተካፍለዋል፡፡
ውይይቱ በዋናነት በአብዬ ግዛት ስለተሰማራው የተመድ ጊዜያዊ የጸጥታ ኃይል ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡
የጸጥታ ኃይሉ አካል ሆኖ በስፍራው የሚገኘው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦር በሱዳን ጥያቄ በቀጣዮቹ ሶስት ወራት ውስጥ ለቆ እንዲወጣ ስምምነት ስለተደረሰባቸው ሁኔታዎች በውይይቱ መነሳቱንም ነው የሃገሪቱ ዜና አገልግሎት (ሱና) የዘገበው፡፡
ተመድ የሱዳንን ሁኔታ ተረድቶ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦር ወጥቶ በሌላ ይተካ የሚለውን ጥያቄ በመቀበሉ ያመሰገኑት መርያም አል ሳዲቅ ሃገራቸው ከደቡብ ሱዳን ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እንደምትሰራ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦር በቶሎ ሊወጣ የሚችልበትን የተቀላጠፈ ሁኔታ ለማመቻቸትም እና ለተተኪው አቀባበል ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡
ሱዳን በጋራ የድንበር ጉዳዮች ላይ ያሉ ጋሬጣዎችን በማጽዳት የራሷን ሚና እንደምትጫወትም ነው ሚኒስትሯ የገለጹት፡፡
በአሀኑ ወቅት ከ3 ሺህ በላይ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሀይል በአብዬ ግዛት እንዳለ የመንግስታቱ ድርጅት ሪፖርት ያስረዳል።
ደቡብ ሱዳን ከሱዳን በህዝበ ውሳኔ ነጻ አገር ለመመስረት መወሰኗን ተከትሎ ነበር የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሀይል ወደ አብዬ ግዛት የተሰማራው።
አብዬ ግዛት በሱዳን እና ደቡብ ሱዳን አዋሳኝ ቦታ የምትገኝ ስትሆን በተፈጥሮ ሀብት የበለጸገች ቦታ መሆኗን ተከትሎ ሁለቱ አገራት በይገባኛል ጥያቄ ምከንያት ወደ ጦርነት እንዳይገቡ በሚል ሰላም አስከባሪ ቦታው ላይ እንዲሰፍር መደረጉ ይታወሳል።
በወቅቱ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሀይል በአብዬ ግዛት ይሰማራልን በሚል ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ጦሩ ወደ ቦታው ሊያቀና ችሏል።
በሱዳን በተቀሰቀሰ የህዝብ ተቃውሞ የቀድሞው ፕሬዘዳንት ኦማር አልበሽር ከስልጣን ከተነሱ በኋላ ስልጣን የያዘው የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ኢትዮጵያ ጦሯን ከአብዬ ግዛት ታስወጣልን የሚል ጥያቄ አቅርቧል።
ኢትዮጵያ በበኩሏ በአብዬ ግዛት የተሰማራው ሰላም አስከባሪ ሀይል መውጣት ካለበት ለከፈለው መስዋዕትነት ተገቢው ክብር ሊሰጠው ይገባል የሚል ጥያቄ አቅርባ ነበር።