ኮሚሽኑ በገዳማይቱ ከተማ ግጭት በነዋሪዎች ላይ እየደረሰ ያለው የህይወት መጥፋትና መፈናቀል እንደሚያሳስበው ገለፀ
ግጭቱ ሳቢያ የተወሰኑ የመተላፊያ መንገዶች በመዘጋታቸው መደበኛ እንቅስቃሴዎች ተገድበዋል
ግጭቱን ለመፍታት የፌደራል መንግስት፣ የአፋርና ሶማሌ ክልል አስተዳደሮች ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጡትም ጠይቋል
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በገዳማይቱ ከተማ ከሐምሌ 17 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በተከሰተው ግጭት በነዋሪዎች ላይ እየደረሰ ያለው የህይወት መጥፋት፣ ንብረት መውደም እና መፈናቀል የሚያሳስበው መሆኑን ገለጸ።
በግጭቱ ምክንያት የሞቱት እና ጉዳት የደረሰባች ሰዎች ሰዎች ቁጥር እንዲሁም የደረሰውን የንብረት ውድመት መጠን በተመለከተ ያለው መረጃ ውስን መሆኑንም ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ይሁንና ግጭቱ በተከሰቱባቸው ቦታዎች እና በአዋኝ ከተሞች የፀጥታ ሁኔታ ወደ ነበረበት ባለመመለሱና የተወሰኑ የመተላፊያ መንገዶች በመዘጋታቸው መደበኛ እንቅስቃሴዎችን ጭምር ገድቧል ብሏል።
ከአካባው ተፈናቅለው ወደ ሙሊ ከተማ እና ወደ ሌሎች ቀበሌዎች ተጠልለው ለሚገኙ ሰዎች የሰብዓዊ እርዳታዎች በአፋጣኝ ማቀረብና እንቅስቃሴ በመገደቡ ምክንያት አቅርቦቱ እንዳይስተጓጎል ጥበቃ ማደረግ ቀዳሚው እምርጃ ሊሆን እንደሚገባም አስታውቋል።
በአካባው በተደጋጋሚ የሚያገረሸውን ግጭት ለመፍታት በፌደራል መንግስት እንዲሁም በአፋርና ሶማሌ ክልል አስተዳደሮች ተገቢውን ትኩረት ሊሰጡት እንደሚገባውም ጠይቋል።
ኮሚሽኑ ግጭቱ በተከሰተባቸው አካባቢዎች በመገኘት አና ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች በመጎብኘት የሚያደርገውን ክትትል የሚቀጥል መሆኑንም አስታውቋል።
በሶማሌ እና በአፋር ክልሎች ሶሞኑን ግጭት መቀስቀሱንና ንፁሃም መሞታቸውን የሶማሌ ክልል ማስታወቁ ይታወሳል።
በሁለቱ ክልሎች መካከል ተፈጥሯል ስለተባለው ግጭት የአፋር ክልል እስካሁን ያወጣው መግለጫ የለም።
በአካባው ያለውን የፀጥታ ችግር ተከትሎም የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር መስመር አክሲዮን ማህበር የካርጎ ትራንስፖርት አገልግሎቱን እንዳቋረ መግለጹም ይታወሳል።