በትግራይ የጋራ ማጣራት ለማድረግ ከኢትዮጵያ የቀረበውን ጥያቄ መቀበላቸውን የተመድ የሰብአዊ መብቶች ኃላፊ ገለፁ
አምነስቲን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት በትግራይን ክልል ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸሙን ሲገልፁ ነበር
ኃላፊዋ በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት አማካኝነት የቀረበውን የ ’አብረን እናጣራ’ ጥሪ በበጎ ተቀብለውታል
በትግራይ ክልል ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀሎችን በተመለከተ ለሚደረገው ማጣራት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ከስምምነት መደረሱን የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኃላፊ ሚሼል ባሽሌት ገለፁ፡፡
በትግራይ ክልል በሰብዓዊነት ላይ ያነጣጠረ የመብት ጥሰት አጋጥሞ እንዲሁም የጦር ወንጀል ተፈጽሞ ሊሆን እንደሚችል በቅርቡ መግለጫ ሰጥተው የነበሩት ኃላፊዋ፣ ጉዳዩን ለማጣራት በኢትዮጵያ መንግስት የቀረበውን ጥሪ መሰረት በማድረግ አብሮ ለመስራት ከስምምነት መድረሳቸውን ነው የሮይተርስ ዘገባ የሚያመለክተው፡፡
የኮሚሽኑ ቃለ አቀባይ ጆናታን ፈውለር እንዳሉት ከሆነ፡ ኃላፊዋ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት አማካኝነት የቀረበውን የ ’አብረን እናጣራ’ ጥሪ በበጎ መልኩ ተቀብለውታል፡፡ ቃል አቀባዩ “የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንና የኢትዮጵያው የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አሁን ላይ ተፈጸመ የተባለውን ምርመራ ለማድረግ የሚያስችል እቅድ ነድፈው ፣ ተልእኮቸቸውን በተቻለ ፍጥነት ለመፈጸም በመስራት ላይ ናቸው”ም ብለዋል፡፡
አምነስቲን ጨምሮ ተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት የትግራይን ክልል ሁኔታ በማስመልከት ከሰብአዊ መበቶች መከበር ጋር ተያይዞ የተለያዩ ሪፖርቶችን ሲያወጡ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ ተፈጸሙ የተባሉት ጥሰቶችና ወንጀሎችን ለማጣራት፣ አለፍ ብሎም ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን ሲገልፅ ቆይቷል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ካስተላለፈው ጥሪ በተጨማሪ ባለፈው ቅዳሜ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በትብብር ለማጣራት መንግስት ዝግጁ እንደሆነ መግለፁም ለዚህ ማሳያ ናቸው፡፡