በምርጫው ወቅት የሕግ አስከባሪ አካላት ሰብአዊ መብቶችን አክብረው እንዲንቀሳቀሱ ኢሰመኮ አሳሰበ
ኢሰመኮ የመብት ጥሰቶች ሲኖሩ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ሲሉም በአጽንዖት ተናገረዋል
ኢሰመኮ በተለያዩ ክልሎች ከሚገኙ የሕግ አስከባሪ አካላት ጋር ምክክር ማድረጉን ገልጿል
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ)በምርጫው ወቅት የሕግ አስከባሪ አካላት ሰብአዊ መብቶችን አክብረው እንዲነቀሳቀሱ አሳሰበ፡፡
ኢሰመኮ ሰኔ 14 ቀን፣ 2013 ዓ.ም. ምርጫ በሚካሄድባቸው ሁሉም ክልሎች ከሚገኙ የሕግ አስከባሪ አካላት ጋር ከሰኔ 2- 5 ድረስ ምክክሮችን ማከናወኑን አስታውቋል፡፡
ምክክሮቹ የተከናወኑት ከአዳማ፣ ከጅማ፣ ከባሕር ዳር፣ ከሃዋሳ፣ ከጋምቤላ፣ ከአሶሳ እና ከሰመራ ከተሞች ፖሊስ እና የፍትህ አካላት ከተውጣጡ መካከለኛ አመራሮች ጋር እንደሆነም ነው ባወጣው መግለጫ ያስታወቀው።
ኮሚሽኑ የምክክር መድረኮቹን ያከናወነው፤ የሕግ አስከባሪ አካላት ካለባቸው ሰብአዊ መብቶችን የማክበር፣ የማስከበር እና የማሟላት ኃላፊነት አኳያ፣ በቅድመ ምርጫው፣ በምርጫው ዕለትና በድኅረ-ምርጫው ወቅት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንዳይፈጸሙ የሕግ አስከባሪ አካላትን ግዴታና ኃላፊነቶች ለማስታወስ እንደሆነም ነው የገለጸው።
ኢሰመኮ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ፣ የመዘዋወር፣ የመሰብሰብ እና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግናሌሎች በምርጫ ወቅት ትኩረት የሚሹ ሰብአዊ መብቶችን በማረጋገጥ ረገድ የህግ አስከባሪ አካላት በሚኖራቸው ሚና ላይ መወያየቱን ገልጿል፡፡
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በምርጫው ወቅት የሕግ አስከባሪ አካላት በገለልተኝነት ተግባራቸውን በመወጣት የዜጎች መብቶችን እንዲያከብሩና እንዲያስከብሩ እንዲሁም ጥሰቶች ሲኖሩ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ በአጽንዖት አሳስቧል።