ከትምህርት ገበታቸው "በኃይል እንዲነጠሉ" የተደረጉ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች እንዲመለሱ እንዲያደርግ ጠቅላይ ም/ቤቱ ትምህረት ሚኒስቴርን ጠየቀ
ጠቅላይ ምክርቤቱ "ከጥር 11/2017 ጀምሮ ዳግም በዲላ ዩኒቨርስቲ ትምህርት እንዳይመሩ" መከልከላቸውን የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት እንዳሳወቀው ገልጿል
ጠቅላይ ምክር ቤቱ ከአለባበስ ጋር በተያያዘ በሙስሊም ሴት ተማሪዎች ላይ የሚደርሰው ከትምህር ገበታ መፈናቀል መፍትሄ አላገኘም ብሏል
የኢትጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት "ከእስላማዊ አለባበስ" ጋር በተያያዘ ከትምህርታቸው የታገዱ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመሰሉ ለትምህርት ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ ጠይቋል።
ጠቅላይ ምክርቤት ትናንት ምሸት በማህበራዊ ገጹ ባወጣው ጥር 15፣2017 ዓ.ም በጻፈው ደብዳቤው ሙስሊም ሴት ተማሪዎች "ከእስላማዊ አለባበስ" ጋር በተያያዘ የሚደርስባቸው "ከፍተኛ ጫናና ከትምህርት መፈናቀል" እንዲቆም ለሚኒስቴሩ ሶስት ጊዜ ደብዳቤ ቢጽፍም መፍትሄ አለማግኘቱን ገልጿል።
ጠቅላይ ምክር ቤቱ በአክሱም ከተማ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች "በሒጃባቸው ምክንያት" ወደ ትምህርት ቤት እንዳይገቡ መደረጋቸውንና እንዲገቡ የተደረገው ጥረት ባለመሳካቱ በመቀሌ ከተማ ሰልፍ መደረጉን ጥር 13፣2017 ዓ.ም በፌስቡክ ገጹ ባጋራው መረጃ ጠቅሷል።
ቀደም ሲል መፍትሄ እንዲሰጥባቸው ያቀረባቸው ጥያቄዎች መፍትሄ አለማግኘታቸውን የገለጸው ጠቅላይ ምክር ቤት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዲላ ዩኒቨርስቲ ተመሳሳይ ችግር አጋጥሟል ብሏል።
ጠቅላይ ምክርቤቱ "ከጥር 11/2017 ጀምሮ ዳግም በዲላ ዩኒቨርስቲ ትምህርት እንዳይመሩ" መከልከላቸውን የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት እንዳሳወቀው ገልጿል።
ትምህርት ሚኒስቴር ከትምህርት ገበታቸው በኃይል የተነጠሉ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርስቲ እንዲገቡ ትዕዛዝ እንዲሰጥና ችግሩን በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲፈታ ምክር ቤቱ የመጨረሻ ያለውን ጥያቄ አቅርቧል።
ትምህርት ሚኒስቴር ጠቅላይ ምክርቤቱ ባነሳቸው ጉዳዮች ዙሪያ በይፋ ያለው ነገር የለም።