ዶናልድ ትራምፕ ሩስያ የዩክሬንን ጦርነት ለማቆም ካልተስማማች ተጨማሪ ማዕቀብ እንደሚጥሉ አስጠነቀቁ
ፕሬዝዳንቱ ከሩስያ በተጨማሪ ማዕቀቡ በአጋሮቿ ላይ እንደሚያነጣጥር ዝተዋል
ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ስልጣን በያዙ በ24 ሰዓት ውስጥ ጦርቱን አስቆማሁ ብለው ነበር
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሩስያ በዩክሬን የምታደርገውን ጦርነት ለማቆም ካልተስማማች ማዕቀብ እና የታሪፍ ጭማሪ ተግባራዊ እንደሚያደርጉ አሳሰቡ፡፡
ፕሬዝዳንቱ በትላንትናው ዕለት ትሩዝ በተሰኝው ማህበራዊ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ “ጦርነቱ በሚቆምበት ሁኔታ ላይ ካልተስማማን ሩስያ እና አጋሮቿ ለአሜሪካ በሚያቀርቡት ማንኛውም ምርት ላይ ታክስ፣ ታሪፍ እና ማዕቀብ ተግባራዊ ከማድረግ ውጭ ሌላ ምርጫ የለኝም” ብለዋል፡፡
የትራምፕ ጽሁፍ በግጭቱ ውስጥ ተሳታፊ ወይም አጋር ናቸው ያሏቸው ሀገራት የትኞቹ እንደሆኑ በይፋ አልገለጸም፡፡
በየካቲት 2022 የተጀመረውን ጦርነት ተከትሎ የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር በሺዎች የሚቆጠሩ ማዕቀቦችን በሩሲያ የባንክ ፣ የመከላከያ ፣ የማኑፋክቸሪንግ ፣ የኢነርጂ ፣ የቴክኖሎጂ እና ሌሎች ዘርፎች ላይ ጥሏል።
በተመድ የሩስያ ምክትል አምባሳደር ዲሚትሪ ፖሊያንስኪ “ትራምፕ በዩክሬን ያለውን ጦርነት ለማቆም ስምምነት ሲሉ የጠሩት ነገር ምን ማለት እንደሆነ እናያለን” ብለዋል፡፡
ፖሊያንስኪ ከሮይተርስ ጋር በነበራቸው ቆይታ ዋናው ጥያቄ ጦርነቱን ማስቆም ብቻ ሳይሆን የዩክሬን ቀውስ ዋና መንስኤ ላይ መፍትሄ መስጠት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ትራምፕ በስልጣን ዘመናቸው በመጀመሪያ ቀን ጦርነቱን እንደሚያስቆሙ በተደጋጋሚ ቢናገሩም በቅርቡ አማካሪዎቻቸው ሂደቱ ወራትን ሊወስድ እንደሚችል አምነዋል፡፡
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የአሜሪካ ግምጃ ቤት የሩስያን የኢነርጂ ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ የሚጎዳ ማዕቀብ በጋዝፕሮም ፣ ኔፍት እና ሰርጉትኔፍቴጋስን በመሳሰሉ የነዳጅ እና ጋዝ አምራቾች ላይ ገቢራዊ አድርጓል፡፡
ትራምፕ ፖሊሲዎቻቸውን ለማስፈጸም ቻይና ፣ ሜክሲኮ እና ካናዳ ላይ ከፍተኛ የታሪፍ ጭማሪ እንደሚያደርጉ እየዛቱ ይገኛሉ፡፡
እነዚያ ሶስት ሀገራት የአሜሪካ ግዙፍ የንግድ አጋር ሲሆኑ በዓመት 2.1 ትሪሊዮን ዶላር የሚያወጣ ንግድ ግንኙነት አላቸው፡፡
በተመሳሳይ በፈረንጆቹ 2014 13.5 ቢሊየን ዶላር የሚያወጣ የነዳጅ ምርት አሜሪካ ከሩስያ አስገብታለች ይህ የዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ወደ ዜሮ ወርዷል፡፡
በ2024 የመጀመሪያዎቹ 11 ወራት አሜሪካ ከሩስያ የምታስገባው ምርት በ2021 ከነበረበት 29.6 ቢሊየን ዶላር ወደ 2.9 ቢሊየን ዶላር ዝቅ ብሏል፡፡
በተጨማሪም ያለቀላቸው ብረቶች ፣ የአሳማ ስጋ እና ሌሎችም ወደ አሜሪካ የሚላኩ ዋና ዋና ምርቶች መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሰዋል፡፡
ሆኖም አሜሪካ አሁንም በግብርና ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውል ጉልህ መጠን ያለውን 1.4 ቢሊየን ዶላር የሚያወጣ ማዳበሪያ ከሩስያ ታስገባለች እንዲሁም ከ 1 ቢሊየን ዶላር ግምት ያለው ለኒዩክሌር ሀይል የሚውል ዩራኒየም ታስገባለች፡፡
ሮይተርስ በሞስኮ እና በዋሽንግተን መካከል ያለው የንግድ ግንኙነት ከጦርነቱ በኋላ በማሽቆልቆሉ የታሪፍ ጫናው ያንያህል ተጽዕኖ ላይኖረው እንደሚችል ዘግቧል፡፡
ነገር ግን ትራምፕ በጦርነቱ ተሳታፊ ናቸው ባሏቸው የሩስያ አጋሮች ላይ እጥለዋለሁ ያሉት ማዕቀብ ከታሪፍ ጭማሪው በበለጠ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል ተብሏል፡፡