ዶናልድ ትራምፕ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት ከገቡ በኋላ ያሳለፏቸው ውሳኔዎች ምን ምን ናቸው?
47ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶናልድ ትራምፕ ስልጣን ከያዙ ሶስተኛ ቀናቸውን ይዘዋል
የስደተኞች ጉዳይ፣የዩክሬን ጦርነት፣የዜግነት እና አየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ አዳዲ ውሳኔዎችን ካሳለፉባቸው ዋነኛ ጉዳዮች መካከል ናቸው
ዶናልድ ትራምፕ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት ከገቡ በኋላ ያሳለፏቸው ውሳኔዎች ምን ምን ናቸው?
ከአራት ዓመት በፊት በተካሄደው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተሸንፈው ወደ ንግዳቸው ተመልሰው የነበሩት ዶናልድ ትራምፕ ዳግም ተወዳድረው 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነዋል፡፡
ከሶስት ቀናት በፊት ቃለ መሀላ ፈጽመው ወደ ነጩ ቤተ መንግስት የተመለሱት ዶናልድ ትራምፕ ስልጣን ከያዙ በኋላ ወዲያውኑ ነበር ውሳኔዎችን ማሳለፍ የጀመሩት፡፡
ዶናልድ ትራምፕ ካሳለፏቸው ውሳኔዎች መካከልም ህጋዊ የመኖሪያ እና ስራ ፈቃድ የሌላቸው ስደተኛ ዜጎችን ማባረር የሚያስችላቸውን ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡
አሜሪካ በስደተኞች ጉዳይ ብሔራዊ አደጋ ተደቅኖባታል በሚል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጁት ዶናልድ ትራምፕ ከሜክሲኮ ድንበር በኩል ተጀምሮ የነበረው የግምብ አጥር እንዲቀጥል፣ ስደተኞችን ወደ መጡበት ማባረር የሚያስችል ስርዓት መዘርጋት፣ ከስደተኞች የተወለዱ ህጻናት የአሜሪካ ዜግነት እንዳያገኙ ማድረግ፣ አሜሪካንን መጎብኘት የሚያስችል ቪዛ ያላቸው ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ እና ሌሎችም ውሳኔዎችን ትራምፕ አስተላልፈዋል፡፡
እንዲሁም በሜክሲኮ በኩል የሚገቡ ስደተኞችን ለማስቆም በዚያው በሜክሲኮ ማቆያ እና ጉዳያቸውን ማየት የሚያስችል ስርዓት እንዲቀረጽም ትዕዛዝ አስተላልፈዋልም ተብሏል፡፡
በሜክሲኮ ድንበር በኩል 11 ሺህ የአሜሪካ ጦር እንዲሰማራ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል የተባለ ሲሆን በቀጣይ ተጨማሪ ወታደሮች ሊሰማሩ እንደሚችሉም ተገልጿል፡፡
በቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከተላለፉ ውሳኔዎች መካከል ከዓለም ጤና ድርጅት መውጣት፣ ከፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት እና በአሜሪካ የተላለፉ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከያ አዋጆች እንዲሻሩም ትዕዛዝ አስተላልፈዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም አሜሪካ የገንዘብ ድጋፍ ከምታደርግባቸው በርካታ ፕሮግራሞች ራሷን እንድታገል እና የበጀት ድጋፍ እንዳይደረግም ውሳኔ አስተላልፈዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የዩክሬን ጦርነት በ100 ቀናት ውስጥ እንዲያበቃ ለሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን ይህ ካልሆነ ግን አዲስ ማዕቀብ በሩሲያ ላይ እንደሚጣልም ትራምፕ ዝተዋል፡፡
የጾታ ቅየራ፣ የዋጋ ንረት መከላከያ፣ የሞት ቅጣት ትግበራ፣በአላስካ አዲስ የነዳጅ ማውጣት ስራ መጀመር እና ቲክቶክን በከፊል አልያም ሙሉ ለሙሉ ለአሜሪካዊያን የሚሸጥበትን ጊዜ ለ75 ቀናት ማራዘም ጉዳይ ዶናልድ ትራምፕ ውሳኔ ያሳለፉባቸው ተጨማሪ አጀንዳዎች ናቸው፡፡