በመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ላይ እየተፈጸመ ያለው ዘረፋ ሀሳብን የመግለጽ መብት ላይ ስጋት መደቀኑን የመገናኛ ብዙኃን ም/ቤት አስታወቀ
ዘረፋው በተቀናጀና በተናበበ መልኩ ተደጋግሞ መፈጸሙ ተራ ዝርፊያ አለመሆኑን አመላክቷል ተባለ
ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ በአራት የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ዝርፊያ መፈጸሙን አስታውቋል
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ም/ቤት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለያዩ ተቋማት ዘረፋ እንደተፈጸመባቸው መሆኑን ገልጾ፤ በዚህም ስራቸውን ለማቆም መገደዳቸውን አስታወቋል።
የህገ መንግስቱን አንቀጽ 29 በመጥቀስ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባልታወቁ ግለሰቦች የሚዲያ ተቋማት እየተዘረፉና መረጃ ለመቀበልና ለማስተላላፍ የሚጠቀሙባቸው መሳሪዎችም እየተወሰዱባቸው በመሆኑ ም/ቤቱ አሳስቦኛል ብሏል፡፡
የመንግስት የጸጥታ አካላት ስራ የሚያስተጓጉል ተመሳሳይ የወንጀል ድርጊት እንዳይፈጸም ተገቢ የሆነ ጥበቃ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ሲል ገልጿል፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ በአራት የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት (በአራት ኪሎ ሚዲያ፣ በ251 ሚዲያና በየኔታ ዩቲዩ፤ በኢትዮጰያ ኢንሳይደር) ላይ የተከሰቱት ዘረፋዎች ጥርጣሬ የሚጭሩ ናቸው ብሏል።
"የቢሮ ዘረፋው የቢሮ በር ሳይሰበር፣ በእረፍት ቀናት፣ በተመረጡ ድርጅቶችና በሚዲያ ቁሳቁሶች ላይ መፈጸሙን ከተቀማቱ ሪፖርት ለመረዳት ችለናል፡፡ በመሆኑም የዘረፋው መደጋገም ድርጊቱ በተራ ግለሰቦች የተፈጸመ ነው ለማለት ጥርጣሬ የሚጭር ሆኗል" ብሏል፡፡
ምርምራ በማድረግ አጥፊዎችን ህግ ፊት የማቅረብ ሂደቱም ዘገምተኛ መሆኑን ጠቅሷል።
ም/ቤቱ ባልታወቁ ሰዎች በተቀናጀና የተናበበ በሚመስል መልኩ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ላይ ተደጋጋሚ ዘረፋ መፈጸሙ ጉዳዩን ይበልጥ አሳሳቢ አድርጎታል፡፡
ዘረፋው የመገናኛ ብዙኃን ባለሞያዎች፣ ድርጅት የማቋቋምና መረጃን ለህዝብ ተደራሽ የማድረግ መብት ላይ ስጋት ደቅኗል ብሏል ም/ቤቱ።