አለማቀፉ የዲጂታል ሚዲያ እና ሳተላይት ኮሙዩኒኬሽን ኤግዚቢሽን በዱባይ ተከፍቷል
በኤግዚቢሽኑ ከ120 ሀገራት የተውጣጡ የብሮድካስት እና ዲጂታል ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው
ዱባይ ከ14 ሺህ በላይ ሰዎች ይጎበኙታል ተብሎ የሚጠበቅውን ኤግዚቢሽን ስታዘጋጅ ለ29ኛ ጊዜ ነው
29ኛው አለማቀፉ የዲጂታል ሚዲያ እና ሳተላይት ኮሙዩኒኬሽን ኤግዚቢሽን በዱባይ ተከፍቷል።
የዱባይ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የቦርድ ዳይሬክተሩ ሼክ ሃሸር ቢን ማክቱም ናቸው ኤግዚቢሽኑን በይፋ የከፈቱት።
ለሶስት ቀናት በሚቆየው ኤግዚቢሽን ከ120 ሀገራት የተውጣጡ ከ340 በላይ በብሮድካስት እና ዲጂታል ሚዲያው ተጽዕኖ መፍጠር የቻሉ አካላት ስራቸውን ለእይታ እያቀረቡ ነው።
በመካከለኛው ምስራቅ እና በአፍሪካ በዲጂታል ሚዲያው የሚፈጠር የስራ እድል ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰም ተሳታፊዎቹ ለጎብኝዎች የራሳቸውን ልምድ እያጋሩ ይገኛሉ።
ኤግዚቢሽኑ በብሮድካስት ሚዲያ የይዘት አዘገጃጀት እና ስርጭት እንዲሁም የዲጂታል ሚዲያ እና መዝናኛ ዘርፎች ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎች ልምድ የሚያጋሩበትና የሚቀስቡበት ይሆናል ተብሏል።
በቀጠናው እና በአለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆኑ እንደ አረብሳት፣ ኢንቴልሳት፣ ኳድሳት ያሉ የሳተላይት እና ስፔስ ቴክኖሎጂ ፈርቀዳጅ ኩባንያዎችም በዱባይ ወርልድ ትሬድ ሴንተር በተከፈተው ኤግዚቢሽን ላይ እየተሳተፉ ነው፡፡
በፊልም ስራ የሚታወቁት እንደ ዋርነርስ ብሮስ እና ዲስከቨሪ ያሉና ሌሎች አለማቀፋዊ ኩባንያዎችም አዳዲስ የሚዲያ ቴክኖሎጂዎችን በዚሁ ኤግዚቢሽኝ ላይ በማስተዋወቅ ላይ ናቸው።
ከኤግዚቢሽኑ ጎን ለጎን ከይዘት ጋር የተያያዙ በዲጂታል ሚዲያው ላይ የተጋረጡ ፈተናዎች ላይ ምክክር ይደርጋል።
የሳተላይት እና ህዋ ቴክኖሎጂን ከሰው ሰራሽ አስተውሎትና ሌሎች ቴክኖሎጂዎች ጋር ማጣመር የሚያስችሉ ሀሳቦች ላይም ከመላው አለም የተሰባሰቡ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ይነጋገራሉ ተብሏል።
ከ29ኛው የዲጂታል ሚዲያ እና ሳተላይት ኮሙዩኒኬሽን ኤግዚቢሽን ባሻገር የመጀመሪያው የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራትን የቴክኖሎጂ ትስስር የሚያሳድግ ኤግዚቢሽን በዱባይ ተከፍቷል።
ሁለቱም ኤግዚቢሽኖች ከ14 ሺህ በላይ ጎብኝዎች እንደሚኖራቸው የሚጠበቅ ሲሆን፥ በመካከለኛው ምስራቅና በአፍሪካ ብሎም በአለም አቀፍ ደረጃ በብሮድካስትና ዲጂታል ሚዲያ የሚሰሩ ባለሙያዎችን የርስ በርስ ግንኙነት እንደሚያሳድጉ ታምኖባቸዋል።