በተወሰኑ የማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ተጥሎ የነበረው የኢንተርኔት እገዳ ተነሳ
እገዳ ተጥሎባቸው የነበሩት ማህበራዊ ሚዲያዎች ያለ ቪፒኤን መስራት ጀምረዋል
እግዱ ተጥሎ የነበረው በፌስቡክ፣ ቴልግራም፣ ዩቲዩብ እና ቲክቶክ ላይ ነበር
በኢትዮጵያ በተወሰኑ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ተጥሎ የነበረው የኢንርኔት እግድ ከወራት በኋላ ተነስቷል።
እግዱ ተጥሎ የነበረው በፌስቡክ፣ ቴልግራም፣ ዩቲዩብ እና ቲክቶክ ላይ ነበር።
እግድ በተጣለበት ወቅት ተጠቃሚዎች ወደ እነዚህ የማህበራዊ ሚዲያዎች ለመግባት ቨርቹዋል ፕራይቬት ኔትዎርክ(ቪፒኤን) ለመጠቀም ተገደው የነበረ ሲሆን ከዛሬ ምሽት ጀምሮ ያለ ቪፒኤን መጠቀም ችለዋል።
በማህበራዊ ሚዲያዎቹ ላይ የኢንተርኔት እገዳ የተጣለው ባለፈው ጥር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ያጋጠማትን ችግር ተከትሎ ነበር።
ሶስት አባቶች በምዕራብ ሽዋ ሀገረስብከት ለ26 ኤጲስ ቆጾሳት ሲመት መስጠታቸውን ተከትሎ ነበር ቤተክሪስቲያ መፈንቅለ ሲኖዶስ ስትል የጠራችው እና በታሪኳ ከባድ የሚባል ፈተና እንዳጋጠማት የገለጸችው።
ይህን ተከትሎ በተለያዩ ቦታዎች በተፈጠሩ ችግሮች በቤተክርስቲያኗ ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ እና የበርካታ ሰዎች ህይወት መጥፋቱ ይታወሳል።
ቤተክርስቲያኗ በወቅቱ መንግስት ህጋዊ ሰውነት ያላትን ቤተክርስቲያን ከጥቃት አልተከላከለም፣ ጣልቃም ገብቷል በማለት ከመንግስት ጋር ቅራኔ ውስጥ ገብታ ነበር።
የኢትዮጵያ መንግስት የጣለውን የእንተርኔት እገዳ እንዲያነሳ ጥሪዎች ቀርበው ነበር።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን(ኢሰመኮ) እና አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተጣለው ገደብ የመናገር መብትን የሚገድብ በመሆኑ እንዲነሳ መጠየቃቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ መንግስት የኢንተርኔት ገደቡ ስለመነሳቱ እስካሁን ያለው ነገር የለም።