ዶ/ር ስለሺ በቀለ ከጠ/ሚ ዐቢይ የተላከ መልዕክት ለሩዋንዳ ፕሬዝደንት አደረሱ
ሁለቱ ሀገራት በከባቢ ጉዳዮች እና በተፈጥሮ ሀብት ዘርፍ መተባበር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያም መክረዋል
ሚኒስትሩ እንዳሉት የሩዋንዳው ፕሬዚደንት “በኢትዮጵያ አቋም ላይ ያላቸውን ተመሳሳይ እይታ እና ድጋፋቸውን ገልጸዋል”
ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለሩዋንዳ ሪፐብሊክ ፕሬዝደንት ፖል ካጋሜ የተላከ ልዩ መልእክት ትናንት ማድረሳቸውን የውሃ ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ስለሺ በቀለ ገልጸዋል፡፡
በትግራይ ክልል ፣ በሕዳሴው ግድብ ፣ በብሔራዊ ምርጫ እና ከሱዳን ጋር ባለው የድንበር ውዝግብ ጉዳይ ለፕሬዝደንት ካጋሜ ገለፃ ማድረጋቸውንም ዶ/ር ስለሺ በትዊተር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡
አክለውም የሩዋንዳው ፕሬዚደንት “በኢትዮጵያ አቋም ላይ ያላቸውን ተመሳሳይ እይታ እና ድጋፋቸውን ገልጸዋል” ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡
በተጨማሪም ከሩዋንዳ አካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር ዶ/ር ጄያን ዲ አርክ ጋር የሁለትዮሽ ውይይት ማድረጋቸውን ነው ዶ/ር ስለሺ የገለጹት፡፡
የሩዋንዳ አካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴርም በትዊተር አድራሻው ፣ በከባቢ ጉዳዮች እና በተፈጥሮ ሀብት ዘርፍ መተባበር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ዶ/ር ስለሺ እና ዶ/ር ጄያን መወያየታቸውን አስታውቋል፡፡
በሕዳሴ ግድብ ጉዳይ አለመግባባት ውስጥ የሚገኙት ኢትዮጵያ ፣ ሱዳን እና ግብፅ ከሚያደርጉት ድርድር ባለፈ አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ ጫና ለማሳደር የተለያዩ አማራጮችን መጠቀማቸውን ቀጥለዋል፡፡
ሦስቱም ሀገራት ወደ ተለያዩ የጎረቤት እና ሌሎች ሀገራት ልዑካንን በመላክ ድጋፍ ለማግኘት ጥረት የሚያደርጉ ሲሆን ፣ በዚህ ረገድ በይበልጥ ግብፅ እና ሱዳን በርካታ ሀገራትን በመዞር ላይ ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም ሁለቱ ሀገራት በተደጋጋሚ የጋራ ወታደራዊ ልምምዶችን አድርገዋል፡፡
ግድቡን በተመለከተ ግብፅ እና ሱዳን አስገዳጅ ስምምነት እንዲደረስ የሚፈልጉ ሲሆን ፣ ኢትዮጵያ በበኩሏ አስገዳጅ ስምምነት የመፈረም ፍላጎት የላትም፡፡
ኢትዮጵያና ሱዳን ከግድቡ በተጨማሪ ከፍተኛ የድንበር ውዝግብ ውስጥም ይገኛሉ፡፡