1496ኛው የነብዩ መሃመድ የልደት በዓል (መውሊድ) እየተከበረ ነው
በዓሉ ሲከበር የነቢዩ መሐመድን በረከቶች በማስተዋልና መንገዳቸውን በማሰብ መሆን አለበት- ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር እድሪስ
መውሊድ አላህ በነቢዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በኩል ለዓለም የሰጠውን በረከት የምናስብበት በዓል ነው- ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ
1496ኛው የነብዩ መሃመድ የልደት በዓል (መውሊድ) በዛሬው እለት በመላ ሀገሪቱ በመከበር ላይ ይገኛል።
1496ኛው የነብዩ መሃመድ የልደት በዓል (መውሊድ) በዓል በተለይም በአዲስ አበባ በታላቁ አንዋር መስጊድ በተለያዩ ሀይማኖታዊ ስነ ስርዓቶች በመከበር ላይ ይገኛል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚደንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር እድሪስ በትናትናው እለት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ምልዕክታቸውም፥ ነቢዩ መሐመድ የተወለዱት መልካም ነገሮችን ሊያስተምሩ፤ መጥፎ ነገሮችን ሊቃወሙ በመሆኑ መልካም ስራቸውን በማየት በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ መውሊድ እንደሚከበር አስረድተዋል።
በዓሉ ሲከበር የነቢዩ መሐመድን በረከቶች በማስተዋልና መንገዳቸውን በማሰብ መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ 1496ኛውን የመውሊድ በዓል አስመልክተው ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክትም፤ “መውሊድ አላህ በነቢዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በኩል ለዓለም የሰጠውን በረከት የምናስብበት በዓል ነው” ብለዋል።
የመውሊድን በዓል ስናከብር የሰው ልጆች ለሌሎች የሰው ልጆች እያደረጉ ያሉትን እዝነት ማስታወስ አለብን። ነቢዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ያደረጉት ነገር ሁሉ ሌሎችን የሰው ልጆች ነጻ የሚያወጣ፣ የሚለውጥና ወደተሻለ ሕይወት የሚመራ ነው። ነቢዩን (ሰ.ዐ.ወ) በዚህ ዕለት የምናስታውሳቸው ከአላህ ተልከው ለሰው ልጆች በፈጸሙት መልካም የመልእክተኛነት አገልግሎታቸው ነው።
በዓሉ የነቢዩ መሐመድን "(ሰ.ዐ.ወ) መልካም አገልግሎት የሚታወስበት መሆኑን የጠቆሙም ሲሆን አዲሱን መንግሥት በድምፁ ያመጣው ሕዝብና አዲሱን አስተዳደር የመሠረተው መንግሥት እነዚህ ነገሮች በእጅጉ ያስፈልጓቸዋል" ብለዋል።