የሱዳን መንግስትን የሚቃወሙ በሺዎች የሚቆጠሩ የሀገሪቱ ዜጎች ካርቱም አደባባይ ወጡ
ጠ/ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ የሱዳን ሽግግር "የከፋ ቀውስ" እንደገጠመው አስታውቀዋል
ሁለቱ የሱዳን ጥምር መንግስት አካላት አሁንም እርስ በእርስ እየተሻኮቱ ነው
የሱዳን ሲቪል አስተዳደር የሚቃወሙ በሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን ዛሬ በካርቱም አደባባይ ሰልፍ መውጣታቸው ተገለጸ።
በሀገሪቱ ዋና ከተማ ካርቱም ቤተ መንግስት በር ላይ ለተቃውሞ የተሰባሰቡት ዜጎች የጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ መንግስት ከስልጣን እንዲለቅ የሚጠይቅ ጥሪ አቅርበዋል።
- የሱዳን ተቃዋሚዎች የቀድሞ አማጺዎችን ጭምር ያካተተ አዲስ ጥምረት መሰረቱ
- የቤጃ ጎሳዎች ፖርት ሱዳንን መዝጋታቸውን ተከትሎ በካርቱም የነዳጅ እና የዳቦ እጥረት ማጋጠሙ ተገለጸ
ትናንት የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ሀገራቸው ወደ ሲቪል አስተዳደር የምታደርገው ሽግግር "የከፋ ቀውስ" እንደገጠመው በማስጠንቀቅ ፍኖተ ካርታ ይፋ አድርገው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ሽግግሩን በተመለከተ ካርቱም የከፋ ቀውስ እንደገጠማት ትናንትና ሲገልጹ ቢቆይም ዛሬ ግን እርሳቸውን የሚቃወም ሰልፍ በካርቱም እየተደረገ ነው።
አሁን ላይ የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቢኔ አንዲሻሻል ሲጠይቅ በአብደላ ሃምዶክ የሚመራው ሲቪል አስተዳደር ደግሞ ጦሩ ስልጣን ፈላጊ እንደሆነ ተስሏል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
ሁለቱ የሱዳን ጥምር መንግስት አካላት አሁንም እርስ በእርስ እየተሻኮቱ ሲሆን ዛሬ ደግሞ በሃምዶክ አስተዳደር ስር ያለው መንግስት ተቃውሞ አጋጥሞታል፡፡
ተቃውሞው ጦሩን የደገፈ እንዲሁም የሲቭል አስተዳደሩን የደተቃመወ መሆኑ ደግሞ በሁለቱ ወገኖች በኩል ያለውን ሽኩቻ እያከረረው እንደሆነም ነው የተገለጸው።
የተቃውሞ ሰልፉ የተዘጋጀው የሱዳኑን የቀደሞ መሪ ኦማር አል በሺርን ከሥልጣን ለማውረድ ለአመጽ የወጡ ቡድኖች እንዲሁም ጦሩን በሚደግፉ የነፃነት እና የለውጥ ኃይሎች መሆኑም ነው የተገለጸው።
ተቃዋሚዎቹ የሲቪል አስተዳደሩ የሚኮንን ጦሩን ደግሞ የሚደግፍ መፈክር ማሰማታቸው ተዘግቧል። በካርቱም የተካሄደው ሰልፍ እስካሁን ባለው መረጃ ምንም አይነት ሁከት ያልነበረው መሆኑን የሱዳን ዜና አገልግሎት ያወጣው ዘገባ ያሳያል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት በሱዳን የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተደርጎ የነበረ ሲሆን ከዚህ ዕለት በኋላ በሽግግር መንግስቱ ውስጥ አለመግባባቶች እያየሉ መጥተዋል ተብሏል።