ፖለቲካ
"እንደሃገር የገጠሙ ፈተናዎችን ለመፍታት ‹በመሥዋዕትነት የታጀበ፤ መልካም አገልግሎት› ያስፈልገናል" - ጠ/ሚ ዐቢይ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የነገውን የመውሊድ በዓል አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል
ዶ/ር ዐቢይ የውስጥ ጠላቶች የገጠሟት ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ እና የኑሮ ውድነት ፈተናዎች ገጥመዋታል ብለዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ "እንደሃገር የገጠሙ ፈተናዎችን ለመፍታ ‹በመሥዋዕትነት የታጀበ፤ መልካም አገልግሎት› ያስፈልገናል" ሲሉ አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ 1496ኛውን የመውሊድ በዓል አስመልክተው ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መግለጫ ‹በመሥዋዕትነት የታጀበ፤ ሕዝብን ሊለውጥ የሚችል መልካም አገልግሎት መስጠት› በእጅጉ ያስፈልገናል ብለዋል።
"ወገኖቻችንን ነጻ ለማውጣት የሚከፈልን መሥዋዕትነት፣ የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን ለመርዳትና ለማቋቋም የሚደረግን መሥዋዕትነት፣ ሀገራችን በርሀብ እንዳትጠቃ በየማሳው የሚደረግን መሥዋዕትነት፣ መልካም አገልግሎት ለሕዝቡ ለመስጠት በየቢሮው የሚደረግን መሥዋዕትነት፣ ሀገራችን በእጅጉ ትፈልጋለች" ሲሉ በመግለጫው ያስቀመጡት ዶ/ር ዐቢይ "በዓሉ የነቢዩ መሐመድን "(ሰ.ዐ.ወ) መልካም አገልግሎት የሚታወስበት መሆኑን የጠቆሙም ሲሆን አዲሱን መንግሥት በድምፁ ያመጣው ሕዝብና አዲሱን አስተዳደር የመሠረተው መንግሥት እነዚህ ነገሮች በእጅጉ ያስፈልጓቸዋል" ብለዋል።
የውስጥ ጠላቶች የገጠሟት ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ እና የኑሮ ውድነት ፈተናዎች ገጥመዋታልም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ያሉት።
"የውስጥ ጠላቶች በፍጥነት አሸንፈን የኢትዮጵያን ኃያልነት ማስፈን፤ በዲፕሎማሲው ረገድ የገጠመንን ፈተና እውነትንና ጥበብን ይዘን ማሸነፍ እንዲሁም የሕዝባችንን የኑሮ ውድነት በላቀ የአመራር ክሂሎት መጀመሪያ ማሻሻል፣ ቀጥሎም መቅረፍ አለብን" ሲሉም አስቀምጠዋል በመግለጫው።
ፈተናዎቹን በድል ለመወጣት "ሲቪሉም ሆነ ወታደሩ መሥዋዕትነት ያለበትን መልካም አገልግሎት" መስጠት እንዳለበትም አሳስበዋል ልክ እንደፈተናው ሁሉ አገልግሎቱ ሁለንተናዊ ሊሆን እንደሚገባ በመጠቆም።
ሦስቱን ፈተናዎች ከመፍታት አንጻር ጦርነቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ በድል የማጠናቀቅ፤ ይቅርታንና አሳታፊ ውይይቶችን የማካሄድ፤ የኢኮኖሚ ፈተናዎቻችንን የሚፈቱ የማክሮና የማይክሮ ኢኮኖሚ ውሳኔዎችን የማሳለፍ ሦስት መንገዶች እንደየሁኔታው ጥቅም ላይ መዋል እንዳለባቸውም አስቀምጠዋል።