1499ኛው የመውሊድ በዓል ተከበረ
በዓሉ በተለይም በአዲስ አበባ በታላቁ አንዋር መስጊድ በተለያዩ ሀይማኖታዊ ስነ ስርዓቶች ተከብሯል
የመውሊድ በዓል በኢትዮጵያ “የሰላሙ ነብይ” በሚል መሪ ቃል ተከብሮ ውሏል
1499ኛውን የነቢዩ ሙሐመድ (ሶ.ዐ.ወ) ልደት (መውሊድ) በዓል በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች አካባቢዎች በሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮች ተከብሮ ውሏል።
በዓሉ በኢትዮጵያ “የሰላሙ ነብይ” በሚል መሪ ቃል የነብዩ መሀመድ (ሰዐወ) በረከቶች በማስተዋል መንገዳቸውን በማሰብ ተከብሯል።
በዓሉ በተለይም በአዲስ አበባ በታላቁ አንዋር መስጊድ በተለያዩ ሀይማኖታዊ ስነ ስርዓቶች ነው የተከበረው።
በሀገር አቀፍ ደረጃ በታላቁ አኑዋር መስጂድ በሚከበረው በዓል በሰደቃ፣ በመንዙማና በነሺዳ በሀይማኖት አባቶች በወጣቶች እና በታዳጊዎች መርሐ ግብር ተከብሮ ውሏል።
የእምነቱ ተከታዮች በዓሉን በመሰባሰብ ሶላት በማድረስ አክብረውታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመብ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት “የመውሊድ በዓል መጠራታችንን የምናስብበት ቀን ነው፤ ነቢዩ መሐመድ (ሰዐወ) የመጡበትን ተልዕኮ፤ የሠሩትን ሥራና ያመጡትን ውጤት እናስባለን” ብለዋል።
“የነቢዩ መሐመድ (ሰዐወ) መምጣት ዓለምን በፊት ከነበረችበት መልክና ጠባይ ቀይሯታል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ “መምጣታቸው የዓለም ታሪክ መክፈያ ሆኗል፤ በዘመናቸው መሥራት ያለባቸውን ሥራም ሠርተዋል” ሲሉም ገልጸዋል።
“በዚህ የመውሊድ በዓል የሕይወት ተልዕኳችንንና የተልዕኳችንን ስኬት እያስተዋልን በዓሉን እንደምናከብር ተሥፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።
“የዘንድሮው በዓል ድርብ በዓል ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ የዛሬ ሃምሳ ዓመት መጅሊስ የተቋቋመው በመውሊድ በዓል ቀን(ረቢ አል አወል 12ኛ ቀን) እንደሆነም አስታውሰዋል።