1497ኛው የመውሊድ በዓል እየተከበረ ነው
በዓሉ በአዲስ አበባ በታላቁ አንዋር መስጂድ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስነ-ስርዓቶች በመከበር ላይ ነው
የመውሊድን በዓል የምናከብረው የዓለምን ታሪክና የሰው ልጆችን ሕይወት በመለውጥ መሆን አለበት- ጠ/ሚ ዐቢይ
1497ኛው የመውሊድ በዓል በእስልምና እምነት ተከታዮች እየተከበረ ይገኛል።
በዓሉ በአዲስ አበባ በታላቁ አንዋር መስጂድ የሃይማኖት አባቶች፣ የእምነቱ ተከታዮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ከማለዳው ጀምሮ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስነ-ስርዓቶች በመከበር ላይ ነው።
በአንዋር መስጂድ እየተከበረ ያለውን በዓል የታላቁ አንዋር መስጂድ ኢማም ሸህ ጣኻ ሀሩር ቁርአን በመቅራትና ዱዓ በማድረግ አስጀምረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመብ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት "በነቢዩ መሐመድ(ሰዐወ) መወለድ ዓለም እጅግ ተጠቅማለች፣ የዓለምን ታሪክ ቀይረዋል፣ የሰው ልጆችንም ሕይወት ለውጠዋል" ብለዋል።
"የመውሊድን በዓል የምናከብረው የዓለምን ታሪክና የሰው ልጆችን ሕይወት በመለውጥ መሆን አለበት" ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል።
"ኢትዮጵያን ከጦርነት በመገላገል ፊታችንን ሙሉ በሙሉ ታሪክና ሕይወት ወደሚለውጡ ዕቅዶቻችን እንዞራለን" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የጀመርነው የሌማት ትሩፋት የቤተሰቦቻችንን ሥርዓተ ምግብ እንዲለውጥ ተግተን እንስራ" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የመውሊድ በዓል በነቢዩ መሐመድ(ሰዐወ) መልካም ተግባራትን የህይወት መርህ ለማድረግ በማሰብ የሚከበር በዓል ነው።
የሰላም፣ የፍትሕ፣ የበጎነትና የአንድነት ፈለጋቸውን መከተል እንደሚገባም ተነግሯል።
በዓሉን በማስመልከት የሀገር መከላከያ ሠራዊት ዛሬ ማለዳ ዘጠኝ ጊዜ መድፍ ተኩሷል።