ሞሮኮ የ2025 የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት ፍላጎት ካሳዩ ሀገራት መካከል ቀዳሚዋ ነች
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የ2025 የአፍሪካ ዋንጫ አስታጋጅነትን ከጊኒ መንጠቁን አስታውቋል።
የካፍ ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ሞሴፔ ባሳለፍነው አርብ የጊኒ ዋና ከተማ ኮናሬን ከጎበኙ በኋላ ባሳለፉት ውሳኔ፤ በጊኒ እንዲደረግ ታስቦ የነበረው የ2025 የአፍሪካ ዋጫ 24 ጨዋታዎች ሙሉ በሙሉ ወደ ሌላ ስፍራ እንደሚዘዋወሩ አስታውቀዋል።
ፕሬዝዳንቱ የ2025 የአፍሪካ ዋንጫ በጊኒ እንዳይካሄድ ካስደረጉ ጉዳዮች ውስጥም ምቹ መሠረተ ልማት እና መገልገያዎች አለመኖርን በምክንያትነት ጠቅሰዋል።
የካፍ ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ሞሴፔ በጉዳዩ ላይ ከጊኒ የሽግግር መንግስት ጋር ከተወያዩ በኋላ በሰጡት መግለጫም፤ የ2025 የአፍሪካ ዋንጫ በጊኒ አይካሄድም፤ ምክንያም ጊኒ ውስጥ ብዙ ዝግጅት ይጎድለናል” ብለዋል።
ከመሰረተ ልማት በተጨማሪም ባሳለፍነው ዓመት የተካሄደውን መፈንቅለ መንግስት ተከትሎ በጊኒ ያለው የፖለቲካ ሁኔታ ከፀጥታ ጋር በተያያዘ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽንን ስጋት ውስጥ መክተቱም ታውቋል።
ደቡብ አፍሪካዊው የካፍ ፕሬዝዳንት ሞቴሴፔ "የካፍ የ2525 የአፍሪካ ዋንጫን ከጊኒ የመንጠቅ ወሳኔ በሀምሌ ወር የተወሰደ መሆኑን እና አሁን ባለው ሁኔታ አዳዲስ አዘጋጅ ሀገራት እንዲወዳደሩ የሚያስችል ሂደት ሊኖር እንደሚገባ ለጊኒ የሽግግር መንግስት ሪፖርት መደረጉን" ተናግረዋል።
በዚህም መሰረት ካፍ ለ2025 የአፍሪካ ሀገራት ዋንጫን ማዘጋጀት የሚፈልጉ ሀገራትን ለማወዳደር ዝግጁ መሆኑን ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።
የዘንድሮ የሴቶች የአፍሪካ ዋጫ ውድድርን የምታስተናደው ሞሮኮ የ2025 የአፍሪካ ዋንጫ አስተናግጅነትን ከጊኒ ለመረከብ ከወዲሁ ፍላጎት ካሳዩ ሀገራት መካከል ቀዳሚ ሆናለች።
የሞሮኮ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምንጮች እንዳረጋገጡት ከሆን፤ ሀገሪቱ የ2025 የአፍሪካ ዋጫን ለማዘጋጀት ለካፍ ማመልከቻ ለማቅረብ ዝግጅት አጠናቃለች።