በግ ከ4 ሺህ እስከ 20 ሺህ ብር ድረስ በመሸጥ ላይ እንደሆኑ ተመልክተናል
በየዓመቱ አዲስ ዓመት መምጣቱን ተከትሎ የሚከበረው የእንቁጣጣሽ በዓል ማድመቂያ ሸመታው ደርቷል፡፡
አል ዐይን አማርኛ በአዲስ አበባ የተለያዩ መገበያያ ስፍራዎች የገበያ ቅኝት አድርጓል።
የሸጎሌ የበሬ ገበያ፣ ሾላ ሁለገብ ገበያ ፣ ጦር ሀይሎች፣ ጃንሜዳ እና በከተማዋ ያሉ ዋና ዋና ሱፐር ማርኬት ስፍራዎች እና በመንግስት ተቋማት የተዘጋጁ የገበያ ማረጋጊያ ገበያዎች ደግሞ የበዓል ገበያ ቅኝት ያካሄድንባቸው አካባቢዎች ናቸው።
የዶሮ፣ በሬ፣ በግ፣ ቅቤ፣ እንቁላል፣ ዘይት፣ ቲማቲም፣ ሽንኩርት እና ሌሎችም ገበያዎች ቅኝቱን ካካሄድንባቸው የሸመታ ስፍራዎች ዋነኞቹ ናቸው።
በዚህም መሰረት የዶሮ እና በሬ ስጋ ገበያዎች በአንጻራዊነት ከአምናው ጋር ተቀራራቢ ዋጋ ያላቸው ሲሆን በግ ከ4 ሺህ እስከ 20 ሺህ ብር እንዲሁም በሬ ከ60 ሺህ እስከ 120 ሺህ ድረስ በመሸጥ ላይ እንደሆኑ ታዝበናል።
የዶሮ ገበያን በሚመለከት በህዝብ መገበያያ ስፍራዎች አንድ ዶሮ ከ400 ብር እስከ 850 ብር ድረስ በመሸጥ ላይ ሲሆን የተበለተ ዶሮ በሱፐርማርኬቶች ላይ ከ400 ብር ጀምሮ በመሸጥ ላይ መሆኑን ተመልክተናል።
ቲማቲም በዘንድሮው ገበያ ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ካሳዩ ምርቶች መካከል ዋነኛው ሲሆን በኪሎ ከ57 ብር አንስቶ እስከ 75 ብር ድረስ በመሸጥ ላይ ከመሆኑ በተጨማሪ ምርቱ በብዙ የገበያ ቦታዎች ላይ እጥረት እንዳለ ተገንዝበናል።
የገበታ ቅቤ በሾላ የሕዝብ ገበያ ለጋ ቅቤ 800 መካከለኛው ቅቤ ደግሞ በ700 ብር ሲሸጥ በሱፐር ማርኬት ስፍራዎች ደግሞ ከ900 ብር ጀምሮ በመሸጥ ላይ ይገኛል።
ሌላኛው የበዓል ማድመቂያ ዘይት ሲሆን አምስት ሊትሩ ከውጭ የገባው እና የሐገር ውስጥ ምርቶች ከ920 ብር እስከ 1200 ብር ድረስ በሁሉም የአዲስ አበባ የግብይት ስፍራዎች በመሸጥ ላይ እንደሆኑ ተመልክተናል።
ሽንኩርት ደግሞ በተለይም በመንግስት ተቋማት አስተባባሪነት የተዘጋጁ የመንገድ ዳር ገበያዎች ላይ በኪሎ ከ35 ብር ጀምሮ በመሸጥ ላይ ሲሆን በሌሎች ስፍራዎች ደግሞ 40 ብር እስከ 50 ብር በመሸጥ ላይ ይገኛል።
የሀበሻ ሽንኩርት ደግሞ በኪሎ በ100 ብር በመሸጥ ላይ ሲሆን ነጭ ሽንኮርት በኪሎ ከ135 ብር እስከ 200 ብር እየተሸጠ መሆኑን ታዝበናል።