‘መንግስት ብር እያተመ ወደ ገበያው መልቀቁን እስካላቆመ ድረስ የኑሮ ውድነቱ አይቆምም’ - የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች
መንግስት እያተመ ወደ ገበያ በሚለቀው ገንዘብ ምክንያት የብር የመግዛት አቅም ስለማነሱ ባለሙያዎች ይናገራሉ
ለመሆኑ የዘንድሮው የበዓል ገበያ እንዴት ነው?
የበዓል ግብይቱ ደርቷል፡፡ በጾምና በጸሎት ያለፉትን ሁለት ሁዳዴ ወራት ያሳለፉ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖችም መጪውን የፋሲካ በዓል ለማክበር ሽር ጉድ ላይ ናቸው፡፡ ገበያው ሞቋል፤ ግብይቱም ደርቷል፡፡ ሆኖም በዓሉን ለማክበር የሚያስፈልጉት መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችና ሸቀጦች ዋጋ ጨምሯል፡፡
ወሳኝ በሆኑ የበዓሉ የፍጆታ እቃዎች ላይ የሚጠየቀው ዋጋ የተጋነነ ነው ሸማቾች እንደሚሉት ከሆነ፡፡ እንደ ሃገር ካጋጠመው የኑሮ ውድነት ጋር ተዳምሮ የናረው የሸቀጦች ዋጋ ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ50 በመቶ የበለጠ ጭማሪ አለው፡፡
በመጋቢት ወር ከፍተኛ ሆኖ የተመዘገበው የምግብ ዋጋ ግሽበትም ከፍ እንዳለ ቀጥሏል፡፡ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ43 ነጥብ 4 በመቶ ጭማሪ አለው ያለለት የምግብ ዋጋ ግሽበት በተያዘው ወርሃ ሚያዚያ እንዳሻቀበ እንደሚቀጥልም ይጠበቃል፡፡
የዛሬ ዓመት በአማካይ በአራት መቶ እና በአምስት መቶ ሲሸጥ የነበረው ዶሮ ዛሬ ከፍ ያለ ዋጋ ይጠየቅበታል፡፡ እንደየ ዝርያውና አካላዊ ይዞታው ቢለያይም እስከ አንድ ሺ አንድ መቶ ብር ዋጋ እንደሚጠራበትም ነው አል ዐይን አማርኛ በየገበያው ተዘዋውሮ ያረጋገጠው፡፡ በግ በአማካይ ከአራት ሺ አምስት መቶ እስከ አስር ሺ ብር እየተጠራበት ነው፡፡ እንቁላል በአማካይ ስምንት ብር ይሸጣል፡፡ ቅቤ ሰባት መቶ ብርና ከዚያ በላይ ነው እየተሸጠ ያለው፡፡ ሽንኩርት እስከ አርባ ብርና ከዚያ በላይ እየተጠየቀበት ይገኛል፡፡ ይህ የፍጆታ እቃዎች ዋጋ እንደናረ መቀጠሉን የሚያሳይ ነው፡፡
የፍጆታ እቃዎች ዋጋ እንዲህ ባሉ ፋሲካን መሰል የበዓል ሰሞናት መጨመሩ የሚጠበቅ ቢሆን ከባለፈው ዓመት በተለየ ለምን በጣም ሊንር ቻለ በሚል አል ዐይን አማርኛ ባለሙያዎችን ጠይቋል፡፡
የምጣኔ ሃብት ጉዳዮች ዘጋቢው ጋዜጠኛ ይስሃቅ አበበ ከበዓሉ ግብይት ጋር በተያያዘ እየታየ ያለው የዋጋ ንረት ሃገሪቱ ካለችበት ወቅታዊ የጸጥታ እና ደህንነት እንዲሁም ምጣኔ ሃብታዊ ይዞታ ጋር የሚያያዝ ነው ይላል፡፡
በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ያጋጠሙ የጸጥታ መደፍረስ ችግሮች የእርድ እንስሳትን ጨምሮ ለበዓሉ ግብዓት የሚሆኑ እቃዎችን እንደ ወትሮው ለማጓጓዝ እንዳላስቻሉ በመጠቆምም ዋጋው ንሯል ይላል ጋዜጠኛው፡፡
ገበያ ከአሁኑም ካለፈውና ከወደፊቱም ጋር የሚያያዝ ነው የሚለው የፍልስፍና ባለሙያው መቆያ ከበደ በበኩሉ ዋናው ችግር ከገበያው ሳይሆን ከመንግስት የሚነሳ ነው ይላል፤ በዚህ የበዓል ወቅት የሚስተዋለው የተጋነነ የሸቀጦች ዋጋ ተያይዞ የመጣ እንጂ አዲስ እንዳይደለ በመጠቆም፡፡
መንግስት በብዛት እያተመ (ከብሔራዊ ባንክ እየተበደረ) ወደ ገበያው በሚለቀው ገንዘብ ምክንያት የመጣ ነው የሚለው ባለሙያው ችግሩ በዋናነት የሚፈታው በራሱ በመንግስት እንደሆነ ይገልጿል፡፡
መንግስት ገንዘብ ማተሙን ማቆም ብቻም ሳይሆን በገበያው ላይ የተበተነውን ገንዘብ ካልሰበሰበ ችግሩ ተባብሶ እንደሚቀጥል አስቀምጧል መቆያ፡፡
መቆያ ‘ነጻነት እና ነጻ ገበያ’ የሚል በፖለቲካ እና በምጣኔ ሃብት ላይ ያተኮረ መጽሃፍን በቅርቡ ለንባብ አብቅቷል፡፡ በመጽሃፉም ዘርዘር ያሉ ምጣኔ ሃብታዊ ጉዳዮችን ዳስሷል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የምጣኔ ሃብት ምሁሩ አጥላው ዓለሙ (ዶ/ር)ም የዋጋ ንረቱ በዓል ስለመጣ ያጋጠመ አይደለም ሲሉ ለአል ዐይን ተናግረዋል፡፡
ይልቁንም ንረቱ መፍትሔ ሳያገኙ ባደሩ መሰረታዊ የምጣኔ ሃብት ችግሮች ምክንያት የመጣ ነው የሚሉት ዶ/ር አጥላው ለንረቱ ዋናው ምክንያት ገንዘቡ ነው ሲሉም ያስቀምጣሉ፤ የመንግስት የገንዘብ ፖሊሲ ሃገሪቱን ለከፋ የዋጋ ንረት እንደዳረጋት በመጠቆም፡፡
ምሁሩ የዋጋ ንረቱን እንደ አንድ ውሃ እንደልቡ እያገኘ እንደለመለመ መስክ ወይም የአበባ ስፍራ (ጋርደን) ይመስሉታል፡፡ ውሃ በጠገበ የአበባ ስፍራ ውሃ መጨመሩ ስፍራውን ቢያጨቀየው እንጂ አበባውን በተለየ መልኩ ሊያፋፋው እንደማይችል በተምሳሌትነት በማንሳትም መንግስት እያተመ ወደ ገበያው የሚለቀው ከኢኮኖሚው የማይመጣጠን ብር የከፋ የዋጋ ንረትን ፈጥሯል ይላሉ፡፡
ማህበረሰቡ እንዲህ ዋጋ በጋሸበበት ሁኔታም ቢሆን አሁንም መሸመቱን ቀጥሏል፡፡ መግዛቱንም አላቆመም፡፡ ይህ በርካታ ገንዘብ ወደ ገበያው በመግባቱ የሆነ ነው እንደ ዶ/ር አጥላው ገለጻ፡፡ በመሆኑም ወደ ገበያ የሚገባው ገንዘብ እስካልተመጣጠነና መሰረታዊ የምጣኔ ሃብት ችግሮቹ እስካልተፈቱ ድረስ ንረቱ አያቆምም፡፡ ከበዓሉ በኋላም ተባብሶ ይቀጥላል፡፡
የዋጋ ንረቱ ያጋጠሙ የጸጥታ ችግሮች በፍጆታ እቃዎች ላይ በፈጠሩት የአቅርቦት ችግር ሳቢያ የተፈጠረ እንደሆነ የጠየቅናቸው ምሁሩ አቅርቦት አልጠፋም ሲሉ ይመልሳሉ፤ በተጋነነ ዋጋም ቢሆን የሚገዙ እቃዎች መኖራቸውን በመጠቆም፡፡
ምርት ባልታጣበትና በቀረበበት ሁኔታ የሚያጋጥም የዋጋ ንረት ከብር የመግዛት አቅም ማነስ ጋር በቀጥታ የሚገናኝ እንደሆነም ዶ/ር አጥላው ለአል ዐይን ተናግረዋል፡፡