የእርድ እንስሳት በቁም በኪሎ ተመዝነው የሚሸጡበት ገበያ
ሽያጩ እንግልትና ወከባን የሚያስቀር ስለመሆኑ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ተናግረዋል
በገበያው በግ በኪሎ 150 በሬ ደግሞ 130 ብር እየተሸጠ ነው
ኢትዮጵያውያን የተለያዩ የበዓል ቀናትን ሲያከብሩ ከሌሎች ቀናት በተለየ መልኩ የእርድ እንስሳትን ሲገዙና ግብይት ሲፈጽሙ ማየት የተለመ ነው፡፡
ልክ እንደሌላው በዓል ሁሉ ኢትዮጵያውያን በተለይም የመዲናዋ አዲስ አበባ ነዋሪዎች የአሁኑን የገናን በዓል ለማክበር አቅማቸው በፈቀደ ሁሉ ለእርድ የሚሆኑ የቁም እንስሳትን ጨምሮ የተለያዩ ግብይቶች እያከናወነ መሆኑን አል-ዐይን ኒውስ ፡በተለያዩ የከተማዋ ስፍራዎች ባደረገው ቅኝት ተመልክቷል፡፡
በሰሚት ኮንደሚንየም አከባቢ ባደረገው ቅኝት በሌላው ጊዜ ከተለመደ የግብይት ሁነት በተለየ መልኩ “የእርድ እንስሳት በቁም በኪሎ ተመዝነው ሲሸጡ”ም አይቷል፡፡
አል-ዐይን ኒውስ በቅኝቱ ቀልቡን የሳበውንና እስካሁን ያልተለመደውን “የእርድ እንስሳት በቁም በኪሎ መዝኖ የመሸጥ ሂደትን” በማስመልከት፤ ለገና በዓል የእርድ እንስሳትን ለተጠቃሚዎች ከሚያቀርበው ሄሎ በግ ትሬዲንግ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
የሄሎ በግ ትሬዲንግ ኃላፊና የኃሳቡ አመንጪ አቶ ዘካርያ አህመድ ይዘውት የመጡትና በኪሎ በተተመነ ቋሚ ዋጋ የቁም እንስሳትን ከነ ህይወታቸው ወደ ማህበረሰብ የማቅረቡ አዲስ ሃሳብ ደምበኞችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብሏል፡፡
“ሄሎ በግ ውጭ ካለው ዋጋ ከ40 እስከ 50 በመቶ ድረስ ቅናሽ አለው፤ ዋና ዓላማው ብዙ በመስጠት ትንሽ ማትረፍን ታሳቢ ደረገ ነው”ም ነው ያሉት አቶ ዘካርያ አህመድ፡፡
አሁን ላይ አንድ በግ በቁሙ ተመዝኖ በኪሎ 150 ብር እንዲሁም በሬ በኪሎ 130 ብር እየሸጡ መሆናቸውም ነው የተናገሩት፡፡
ስራው ከተጀመረ 3ኛ ቀኑ አስቆጥሯል ያሉት አቶ ዘካርያ፤ በቀን በአማካይ ከ500 በላይ ደምበኞችን ሰሚት ኮንዶሚኒየም ጊዮርጊስ ቤተ ክርስትያን አካባቢ በሚገኘው የግብይት ስፍራቸው እያስተናገዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አል ዐይን ግዢ ሲፈጽሙ ያገኛቸው ተጠቃሚዎች በበኩላቸው ሄሎ በግ ይዞት በመጣው አዲስ የግብይት ሃሳብ ደስተኛ ነን ብለዋል፡፡
ተጠቃሚዎቹ “ሄሎ በግ ከደላላ፣ ከጭቅጭቅ፣ ከወከባ እና ግርግር የሚያስቀር አዲስ እና ዘመናዊ ሃሳብ ይዞ በመምጣቱ ደስተኞች ነን” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ይህ አዲስ የእርድ እንስሳት የግብይት መንገድ ገዢ የፈለገውን በቀላሉ ገዝቶ ለመሄድ የሚያስችል እንደሆነም ነው የገለጹት፡፡