በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በተፈጠረው ችግር ላይ የመንግስት ምላሽ ምን ይሆናል?
ቤተ ክርስቲያኗ ከስርዓት ውጪ የጵጵስና ሹመት የሰጡ ግለሰቦች የሰጠኋቸውን ክህነት አንስቻለሁ መንግስትም ህግ ያስከብር ብላለች
መንግስት ሕጋዊ ሰውነት ያላት የቤተ ክርስቲያኗን ውሳኔዎች የማክበርና የማስከበር ግዴታ አለበት- የህግ ባለሙያ
ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አገልጋይ የነበሩ አባቶች ለ26 የሀይማኖት አባቶች የጵጵስና ሹመቶችን ሰጥቻለሁ ማለታቸውን ተከትሎ ነበር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ላይ ችግር መፈጠሩ የተገለጸው።
ይህ የትይዩ ጵጵስና ሹመት የተሰጠው በቀድሞ ማዕረጋቸው አባ ሳዊሮስ በሚል ይጠሩ የነበሩ የቤተ ክርስቲያኗ አገልጋይ ነበር።
ቤተክርስቲያኗ እኝህ የሀይማኖት አባት ከህግ እና ስርዓት ውጪ የጵጵስና ሹመቶችን በመስጠታቸው ምክንያት እና ይህንን ሹመት በተቀበሉ ሀይማኖተኛ ሰዎች ላይ ከዚህ በፊት ሰጥታው የነበረውን ሀይማኖታዊ ማዕረግ ወይም ክህነታቸውን አንስቻለሁ፣ የቤተ ክርስቲያኗን ንብረት እና ማዕረግም መጠቀም አይችሉም ስትል በይፋ አሳውቃለች።
ከክህነታቸው የታገዱት እነዚህ የቀድሞ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ ቀርበው በሰጧቸው ቃለ መጠይቆች ላይ የጀመሯቸውን ስራዎች እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንም መንግስት ህግ እንዲያስከብር ማሳሰቧ እና የታገዱት የቀድሞ የቤተ ክርስቲያኗ አገልጋዮች እቅዳችንን ለማስፈጸም ስራችንን እንቀጥላለን ማለታቸውን ተከትሎ ጉዳዩ ትኩረትን ስቧል።
አል ዐይን አማርኛ በቀጣይ ሊደረጉ የሚችሉ ጉዳዮች ምን ምን ሊሆኑ ይችላሉ? መንግስትስ ህግ ሲያስከበር በምን መንገድ ሀላፊነቱን ሊወጣ ይችላል? ሲል የህግ ባለሙያዎችን አስተያየት ጠይቋል።
ጠበቃ እና የሕግ ባለሙያው አቤል ዘውዱ በዚህ ጉዳይ የመንግስት ምላሽ ሕግን ከማስከበር አንጻር ምን ሊሆን ይችላል? በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄ የመንግስት የመጀመሪያው ሃላፊነት በሐይማኖት እና በመንገስት መካከል የተሰመረውን ቀይ መስመር ማክበር ነው ብለዋል።
መንግስት በየትኛውም ሀይማኖት ጣልቃ አይገባም፣ ኃይማኖትም በመንግስት ስራዎች ላይ ጣልቃ አይገባም በሚል በኢፌድሪ ሕገ-መንግስት ላይ በጉልህ መጻፉን የጠቀሱት ጠበቃ ሔኖክ መንግስት ይሄንን ጉልህ ህግ ካላከበረ ዜጎችን የህግ የበላይነትን አክብሩ የማለት መብቱን ሊያጣ ይችላልም ብለዋል።
ሁለተኛው የመንግስት ኃላፊነት ሕጋዊ ሰውነት ላላት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ንብረቶች፣ አገልግሎት እና ሌሎች በህግ የተመዘገቡ ሀብቶችን እና ተቋማትን ከጉዳት እንዲጠበቁ ማድረግ እንደሆነ የሕግ ባለሙያው ጠቅሰዋል።
ጠበቃ አቤል አክለውም ማንኛውም ግለሰብ የፈለገውን ሀይማኖት የመከተል መብት አለው ነገር ግን በአንድ ሐያማኖት መካከል መከፋፈል ሲፈጠር ተቋሙ በራሱ ችግሩን እንዲፈታ መተው አንዱ መፍትሄ ቢሆንም፤ አለመስማማቱ ከቀጠለ ግን ህጋዊ ሰውነት ላለው ተቋም ህጋዊ ከለላ መስጠት፣ ንብረቶችን ከዘራፊዎች መጠበቅ የመንግስት ግዴታ ነውም ብለዋል።
ሌላኛው የሕግ ባለሙያ እና ጥናት አማካሪው ቶማስ ታደሰ በበኩላቸው የቀድሞው የፌደራል ጉዳዮች የአሁኑ ሰላም ሚኒስቴር የሚያስፈጽመው በ2012 ዓ.ም መመሪያ ቁጥር 19/2012ትን ማክበር እንዳለበት አሳስበዋል።
ትይዩ ጵጵስና የሰጡ ግለሰቦች በቀጣይ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎቶችን እንስጥ፣ የባንክ አካውንቶችን እናንቀሳቅስ፣ ንብረቶችን እንጠቀም ሊሉ እንደሚችሉ ይጠበቃል የሚሉት ባለሙያው ይህ ግን ከህግ አንጻር ትክክል አይሆንም፣ የመንግስትም ዋና ኃላፊነት የሚሆነው ህጋዊ ሰውነት ላለው ተቋም ህጋዊ ከለላ እና ጥበቃ ማድረግ ይሆናልም ብለዋል።
በመመሪያ ቁጥር 19/2012 መሰረትም የሐይማኖት አባቶች ወንጀል እንዲፈጸም ማነሳሳት፣ ህጋዊ ሰውነት ያለው እና የሌላን የሀይማኖት ተቋም አርማ፣ ንብረት፣ አልባሳት እና ሌሎች ንብረቶችን እንዳይጠቀሙ ይደነግጋል።
በዚህ መመሪያ መሰረትም እነዚህ የትይዩ ጵጵስና ሹመት የሰጡ የቀድሞ የቤተ ክርስቲያኗ አገልጋዮች አዲስ የሀይማኖት ተቋም የመመስረት እንጂ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን ንብረቶች እና ሀብቶችን የመጠቀም ምንም አይነት ህጋዊ መብት እንደሌላቸው፣ እንጠቀም ካሉም ግጭት ሊከሰት ስለሚችል እና ግጭቱ እንዳይከሰት መንግስት የቤተ ክርስቲያኗን ውሳኔዎች የማክበር እና የማስከበር ግዴታ እንዳለበት ባለሙያው ጠቅሰዋል።
ይህ በዚህ እንዳለም ትይዩ የጵጵስና ሹመቶችን ለሰጡ እና ሹመቱን ለተቀበሉ የቀድሞ የቤተ ክርስቲያኗ አባቶች ማንኛውም አደጋ ከየትኛውም ወገን እንዳይደርስባቸው የመጠበቅ ግዴታም የመንግስት እንደሆነ ተናግረዋል።
በቅርቡ በተወሰኑ የቀድሞ የቤተ ክርስቲያኗ አገልጋዮች አማካኝነት የተፈጸመው ድርጊት የሀይማኖቱን ተከታዮች ሊከፋፍል እና ግጭት እንዲከሰቱ ሊያደርጉ ይችላሉ ያሉት የህግ ባለሙያው ከእንግዲህ ትልቁን ስራ የሚወስደው በብቸኝነት ህግን የማስከበር ስልጣን ያለው መንግስት መሆኑንም አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም ከቤተ ክርስቲያኗ ህግ ውጪ ተካሂደዋል ባለቻቸው የጵጵስና ሹመቶች ዙሪያ ውሳኔ ማሳለፏ ይታወሳል።
በዚህ መሰረትም 1ኛ አባ ሳዊሮስ፣ 2ኛ አባ ኤዎስጣቴዎስ እና 3ኛ አባ ዜና ማርቆስ ሥልጣነ ክህነታቸውና የማዕረግ ስማቸው በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ውሳኔ መነሳቱ ተገልጿል።
ሶስቱ የቤተክርስቲያኗ የሀይማኖት አባት የነበሩት ሰዎችም ከጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በቀድሞ ዓለማዊ ስማቸው እንዲጠሩ መወሰኑን ቅዱስ ሲኖዶስ ማሳወቁ ይታወሳል።
የመንግስት ኮሙንኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ባሳለፍነው ሳምንት ሰማያዊ ባጅ ባለው የፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ በድርጊቱ ማዘናቸውን ገልጸው “የእምነቱ ተከታይ አባቶች ሁኔታውን በስክነትና ቤተ-ክህነታዊ ስርዓት እንዲፈቱ ጉዳዩን ለነሱ መተው እጅጉን አስፈላጊ ነው” ብለዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም ጉዳዩን “አባቶች በትዕግሥት እና ሃይማኖታዊ ስርዓት ችግሩን ይፈታሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ጉዳዩን የተለያየ ፖለቲካዊ እና አካባቢያዊ ገፅታ መስጠትም ተገቢ አይደለም” ሲሉም አክለዋል።