የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ወደ ጦርነት የገቡ አካላትን ለማስታረቅ ጠየቀች
ላለፉት 15 ቀናት ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተጠናቋል
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በትግራይ ላሉ የሀይማኖት አባቶች ጥሪ አቀረቡ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ወደ ጦርነት የገቡ አካላትን ማስታረቅ እንደምትፈልግ ገለጸች፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቷ ከግንቦት 9 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ስታካሂድ የነበረውን የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ማህበራዊና መንፈሳዊ ውሳኔዎችን በማሳለፍ አጠናቃለች፡፡
የጉባኤውን መጠናቀቅ ተከትሎም ቤተ ክርስቲያኒቷ ውሳኔዎቿን የተመለከተ መግለጫን አውጥታለች፡፡
በመግለጫው በኢትዮጵያ በጦርነት ውስጥ ያሉ ወገኖች ወደ ሰላም እና እርቅ እንዲመጡ ማስታረቅ እንደምትፈልግ አስታውቃለች፡፡
ምልዓተ ጉባኤው በአሁኑ ደረጃ በኢትዮጵያ ባለው የሰላም እጦት ላይ በሰፊው መወያየቱን ገልጻ በቀጣይ ጦርነትና የእርስ በርስ ግጭት ተወግዶ አጠቃላይ ሰላም በሚሰፍንበት መልኩ ተነጋግሮ ችግሩን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍታት እንዲቻል፣ የአስታራቂነት ሚናዋን መጫወት እንድትችል ለማድረግ ለፌዴራል መንግሥት ጥያቄ አቅርቤያለሁ ብላለች፡፡
እንዲሁም በቤተ ክርስቲያናንና በኢትዮጵያ እንደ ሀገር የተከሰተውን የሰላም እጦት ተከትሎ የደረሰው ሕልፈተ ሕይወት፣ የካህናትና የምእመናን ሞት እና የአብያተ ክርስቲያናት መቃጠል ላይ ጉባኤው መክሮ ችግሩ መፍትሔ እንዲያገኝ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት እንዲቀርብ ተደርጓልም ተብሏል በመግለጫው፡፡
በበዓል ማክበሪያ ቦታዎች መነጠቅ ዙሪያ አጥፊዎች ለሕግ እንዲቀርቡ፣ በቀጣይም በመንግሥት በኩል አስፈላጊው ጥበቃ እንዲደረግላት ቤተክርስቲያኒቱ መጠየቋንም ነው የገለጸችው፡፡
በተጨማሪም እስካሁን በቤተ ክርስቲያን ላይ ደረሰ የተባለው ችግር በአይነትና በቁጥር ተለይቶ ለሚመለከታቸው የፌዴራልና የክልል መንግሥት አካላት ቀርቧልም ተብሏል፡፡
ቤተክርስቲያኒቷ አክላም በወቅታዊ ችግር ምክንያት ችግር ለደረሰባቸው፣ ለተፈናቀሉና ለተሰደዱ ወገኖች፣ ለፈረሱና ለተቃጠሉ አብያተ ክርስቲያናት ማቋቋሚያ፣ ለተዳከሙ የአብነት ትምህርት ቤቶች መደጐሚያ የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግ መወሰኗንም ገልጻለች፡፡
ቤተክርስቲያኒቷ በትግራይ ክልል ለሚገኙ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትም ጥሪ አቅርባለች፡፡
ምልዓተ ጉባኤው ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳቱ ቤተ ክርስቲያኒቱን አስመልክተው ታህሳስ 30 ቀን 2014 ዓ/ም እና የካቲት 3 ቀን 2014 ዓ/ም ያወጡትን መግለጫ መገምገሙ የተገለጸ ሲሆን በቀጣይ የክልሉ አባቶች በማዕከል እንደ ቅዱስ ሲኖዶስ አባልነታቸው ለአገር አንድነት እና ሰላም በጋራ እንዲሠሩ ጥሪ ቀርቧል፡፡
እንዲሁም ቤተክርስቲያኗ በምልዓተ ጉባኤው ላይ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት የሚሰጥ የሕክምና ማዕከል እንዲቋቋም ስለመወሰኗ በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡
ትናንት ረቡዕ የባሕርዳር እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆኑትን ብፁዕ አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ እንዲሁም የየኒዮርክ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ/ር) የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ በመሆን በጉባዔው መመረጣቸው ይታወሳል፡፡