የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሶስት የሀይማኖት አባቶችን ማዕረግ አገደች
የክህነትና ማዕረግ ስልጣናቸው የታገደባቸው አባቶች ከሰሞኑ የጵጵስና ሹሙት ጋር በተያያዘ ነው
ቤተክርስቲያኗ ከሰሞኑ ከህግ ውጪ ተካሂደዋል በተባሉ የጵጵስና ሹመቶች ዙሪያ ውሳኔ አሳልፋለች
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሶስት የሀይማኖት አባቶችን ማዕረግ አገደች።
ቤተክርስቲያኗ ከሰሞኑ ከህግ ውጪ ተካሂደዋል በተባሉ የጵጵስና ሹመቶች ዙሪያ ውሳኔ ማሳለፏን ገልጻለች።
በዚህም መሰረት 1ኛ አባ ሳዊሮስ፣ 2ኛ አባ ኤዎስጣቴዎስ እና 3ኛ አባ ዜና ማርቆስ ሥልጣነ ክህነታቸውና የማዕረግ ስማቸው በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ውሳኔ መነሳቱ ተገልጿል።
ሶስቱ የቤተክርስቲያኗ የሀይማኖት አባት የነበሩት ሰዎችም ከጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በቀድሞ ዓለማዊ ስማቸው እንዲጠሩ መወሰኑን ቅዱስ ሲኖዶስ አሳውቋል።
በቤተ ክርስቲያኗ መንፈሳዊ አገልግሎት ዙርያም በሕይወትም ሆነ በሞት ማናቸውንም መንፈሳዊ አገልግሎት እንዳያገኙ ቅዱስ ሲኖዶስ አውግዞ ከቤተ ክርስቲያን እንደለያቸውም መወሰኑ ተገልጿል።
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ አውግዞ በለያቸው ግለሰቦች ይመሯቸው በነበሩ አህጉረ ስብከት መንፈሳዊ አገልግሎት በማከናወን ሀገረ ስብከቱን የሚመሩ ብፁዐን አባቶች ማለትም ለደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ፣ለኬንያ፤ኡጋንዳ፤ታንዛኒያ እና ሩዋንዳ ሀገረ ስብከት ፣ ለኢሉ አባቦራ እና በኖ በደሌ ሀገረ ስብከት ፣
በሰሜን አሜሪካ ለሜኒሶታ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት፣ ለጉጂ፤ ምዕራብ ጉጂ እና ቦረና ሊበን ዞኖች ሀገረ ስብከት ለምስካዬ ኅዙናን መድኃኒዓለም ገዳም በአባትነት የሚመሩ አበው ሊቃነ ጳጳሳት እንዲመደቡ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ወስኗልም ተብሏል፡፡
ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በመጣስ በኤጲስ ቆጶስነት የተሸሙ 25 መነኰሳት በሕገ ወጥ መንገድ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንንን ጥሰው የተገኙ በመሆኑ አስቀድሞ ከቤተ ክርስቲያን የተሰጣቸው ከዲቁና ጀምሮ ያለው ሙሉ ሥልጣነ ክህነት ተሽሮ ከዛሬ ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ተወግዘው ከቤተ ክርስቲያን መለየታቸውንም አስታውቋል።
ቅዱስ ሲኖዶስ " በስም ተጠቅሰው የተወገዙት ግለሰቦች በሠሩት የቀኖና ጥሰት ተጸጽተው ይቅርታን ቢጠይቁ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምህረት ደጆች ሁል ጊዜ ክፈት መሆናቸውና በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት እንቀበላቸዋለን" ብሏል።
የተከሰተውን ችግር አስመልክቶ ዝርዝር ጥናት እና የመፍትሔ ሐሳብ የሚያቀርብ አንድ ዐቢይ ኮሚቴ በቋሚ ሲኖዶስ እንዲሰየም ሲኖዶሱወስኗል።
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ያሳለፈውን ውሳኔ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀምሮ በየደረጃው ላሉት የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች እንዲከናወኑ እና ይህ ውሳኔ ከሸኚ ደብዳቤ ጋር እንዲደርሳቸው መወሰኑም ታውቋል።