በህገወጥ መንገድ ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት ተጽሞላቸው የነበሩ 17 የቀድሞ አባቶች የይቅርታ ደብዳቤ አስገቡ
ቀሪዎቹ ስድስት የቀድሞ አባቶች በቅርቡ ደብዳቤውን ያስገባሉ ተብሏል
ቤተ-ክርስቲያኒቱ ከቀናት በፊት የቀድሞ አባቶች በይቅርታ ከመመለሰ ይልቅ ሹመታቸው እንዲጸድቅላቸው ጠይቀዋል ብላለች
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ከቀድሞ አባቶች ጋር የተደረሰውን ስምምነት የተቀበሉ 17 አባቶች የይቅርታ ደብዳቤ ማስገባታቸውን አስታወቀች።
17ቱ የቀድሞ አባቶች ባለ 10 ነጥብ ስምምነቱን መቀበላቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ለቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ማስገባታቸውን ማህበረ ቅዱሳን ብሮድካስት አገልግሎት ዘግቧል።
በተጨማሪም አንድ አባት ደብዳቤ የላኩ ሲሆን ቀሪዎቹ ስድስት የቀድሞ አባቶች በህመም ምክንያት አልተገኙም የተባለ ሲሆን፤ "በቅርቡ ማመልከቻ ይዘው ይመጣሉ" ተብሏል።
- ቤተ ክርስቲያኗ "ህገ ወጥ" የተባሉ የቀድሞ አባቶችን በተመለከተ ያሳለፈችው ሦስት ውሳኔዎችን ምንድን ናቸው?
- የትግራይ አህጉረ ስብከት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስርዓትን እንዲያከብር ቋሚ ሲኖዶስ ጠየቀ
ባለፈው ቅዳሜ የቀድሞ አባቶች በይቅርታ ከመመለሰ ይልቅ ሹመታቸው እንዲጸድቅላቸው መጠየቃቸውን ቤተ-ክርስቲያኒቱ ገልጻ ነበር።
ይህን ጥያቄ አልቀበልም ያለችው ቤተ- ክርስቲያኒቱ፤ የቀድሞ አባቶችን በተመለከተ ሦስት ውሳኔዎችን ወስናለች።
ጥር 14፤ 2015 ዓ.ም ሦስት ጳጳሳት በምስራቅ ሽዋ በሚገኝ ሀገረ-ስበከት 25 ኤጲስ ቆጶሳት ሾመናል ማለታቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ስርዓቷና ህጓ መጣሱን ማሳወቋ አይዘነጋም።
ቤተክርስቲያኗ አስቸኳይ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ አድርጋም ሲመት የሰጡትን እና የተቀበሉትን በሙሉ ከቤተክርስቲያን እንዲለዩ እና እንዲወገዙ ውሳኔ ውሳኔ ማሳለፏ ይታወሳል።
ቅዱስ ሲኖዶስ በወቅቱ "በስም ተጠቅሰው የተወገዙት ግለሰቦች በሠሩት የቀኖና ጥሰት ተጸጽተው ይቅርታን ቢጠይቁ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምህረት ደጆች ሁልጊዜ ክፍት መሆናቸውና በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት እንደምትቀበላቸው" መግለጹ አይዘነጋም።
በዚህም መሰረት ቤተክርስቲያኗ የይቅርታ ደብዳቤ የሚያስገቡ አባቶችን እየተቀበለች ትገኛለች።