ቤተ ክርስቲያኗ "ህገ ወጥ" የተባሉ የቀድሞ አባቶችን በተመለከተ ያሳለፈችው ሦስት ውሳኔዎችን ምንድን ናቸው?
የቀድሞ አባቶች በይቅርታ ከመመለሰ ይልቅ ሹመታቸው እንዲጸድቅላቸው መጠየቃቸውን ቤተ ክርስቲያኗ አስታውቃለች
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ቤተ- ክርስቲያኒቱ የሹመት ጥያቄውን አልቀበልም ብላለች
መጋቢት 16 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና በህገ-ወጥ መንገድ ተሾመዋል የተባሉ የቀድሞ አባቶች "ስድስት ተወካዮች" መካከል ውይይት ተካሂዷል።
ውይይቱን አስመልክተው መግለጫ የሰጡት የቤተ-ክርስቲያኒቱ ህዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ ሊቀ ሥዩማን እስክንድር ገብረ ክርስቶስ፤ መጋቢት ስድስት ቅዱስ ሲኖዶስ ለቀድሞ አባቶች የይቅርታ መጠየቂያ የአምስት ቀናት ቀነ-ገደብ ማውጣቱን ገልጸዋል።
በዚህም ከይቅርታ ማመልከቻ ይልቅ ቤተ-ክርስቲያኒቱ ህገ-ወጥ ያለችው ሹመተ ጵጵስና እንዲጸድቅላቸው መጠየቃቸውን ኃላፊው ተናግረዋል።
- በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በተፈጠረው ችግር ላይ የመንግስት ምላሽ ምን ይሆናል?
- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን መንግስት አቋሜን ተቀብሏል አለች
"የቤተ-ክርስቲያን የፍቅርና ይቅርታ እጅ በግለሰቦቹ እንደመልካም አልታየም" ብለዋል።
"ስምምነቱን በመርህ ደረጃ እንቀበለዋለን በአፈጻጸም ደረጃ ግን ቅዱስ ሲኖዶስ ሹመታችንን ያጽድቅልን" የሚል ጥያቄ ማቅረባቸውን የመምሪያው የኃላፊ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ከዚህ በኋላ ህገ-ወጥ ያለቻቸውን የቀድሞ አባቶችን በተመለከተ ሦስት ውሳኔዎችን መወሰኗን አስታውቀዋል።
በዚህም መሰረት፤
1.በየትኛውም መንገድ የጋራ ውይይት አይኖርም
2.ለይቅርታ የሚመጡ ከሆነ በቡድን ተሰባስቦ ሳይሆን በግለሰብ ደረጃ እንዲሆን
3.የይቅርታ ማመልከቻውን እያንዳንዳቸው ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽህፈት ቤት ማስገባት ይኖርባቸዋል።
ቅዱስ ሲኖዶስ በዚህና በሌሎች መሠረታዊ የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ መጋቢት 21፤ 2015 ዓ.ም ምልዓተ ጉባኤ ተጠርቷል።