የኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የህዝብ ለህዝብ የሰላም ኮንፈረንስ እየተካሔደ ነው
ዛሬ ታህሳስ 16 ቀን 2012 ዓ.ም በአሶሳ የተካሄደው ኮንፈረንስ በሁለቱ ክልሎች የጋራ ሰላምና ልማት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሲሆን የሁለቱን ክልሎች ሰላም ማጠናከርና የጋራ ልማት ጉዳይ ላይ ያተኮረ ነው፡፡
የአሶሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ኡመር አህመድ በኮንፈረነሱ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ለዘመናት አብሮ የመኖር እሴት ያለውን የሁለቱን ክልሎች ህዝብ ለማጋጨትና ጉዳት ለማድረስ የተደረገው ሙከራ በህዘቡና በሁለቱ ክልሎች አመራሮች ቁርጠኝነት በመክሸፉ ሁለቱ ክልሎች ወደ ቀድሞ ሰላማቸው መመለሳቸውን ተናግረዋል፡፡ የተጀመረውን ለውጥና የብልፅግና ጉዞ ከግብ በማድረስና ተጠቃሚ ለመሆን ሁሉም እጅ ለእጅ በመያያዝ መስራት እነዳለበትም ከንቲባው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በሁለቱ ክልሎች መካከል ተፈጥሮ የነበረው አለመግባባትና የሰላም መደፍረስ ወደ ቀድሞ ሰላማዊ ቦታው መመላሱንና በተፈጠረው ችግር ከሁለቱም ክልሎች ከመኖሪያ ቄዬያቸው ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎች ወደ ቄዬያቸው መመላሳቸዉንም ከሁለቱ ክልሎች የጋራ ሰላምና ልማት ማስተባብሪያ ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ከሁለቱም ክልሎች ተፈናቅለው ቤታቸው ለተቃጠለባቸዉ 500 ሰዎችም በኢትዮጽያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ነቀምቴ ቅርንጫፍ የቤት ግምባታው እየተካሄደ ነው፡፡ የሁለቱ ክልሎች ህዝቦች የሁለቱንም ባህል እና እሴት በማወቅ በወንድማማችነት ስሜት አብረው እንዲሰሩም እየተሰራ መሆኑ በኮንፈረንሱ ተጠቅሷል፡፡
በዚህም መሰረት በቤኒሻነጉል ጉሙዝ ክልል ዞኖችና መተከል ወረዳ 41 የአፋን ኦሮሞ ትምዕርት ቤቶች ተከፍተዉ አገልግሎት እየሰጡ ነዉ፡፡በሁለቱ ክልሎች ድምበር ላይ የሚገኙ ማህበረሰቦችንም በመሰረተ ልማት ለማስተሳሰር የአርጆ-ጂማ-ሶጌ 47 ኪ/ሜ መንገድ እና ሀሮ ሊሙ-ሶጌ-ያሶ 20 ኪ/ሜ መንገድ በጥቅሉ ከ200 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ እተገነባ ነዉ፡፡
ምንጭ፡- ኦቢኤን