የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የቀጥታ ቴሌቭዥን ስርጭት እና የውድድር ስያሜ በ22.5 ሚሊዮን ዶላር ተሸጠ
ሊጉ ታህሳስ 03/2013 ዓ.ም እንደሚጀመር የስፖርት ኮሚሽን መግለጹ ይታወቃል
የውድድሩን የቴሌቭዥን ስርጭት እና የውድድር ስያሜ መልቲ ቾይዝ ኢትዮጵያ ለ5 ዓመት ገዝቷል
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የቀጥታ ቴሌቭዥን ስርጭት እና የውድድር ስያሜ በ22.5 ሚሊዮን ዶላር ተሸጠ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሼር ካምፓኒ የፕሪሚየር ሊግ ውድድሩን በቀጥታ ቴሌቪዥን ስርጭት ለማስተላለፍ ፍላጎት ያላቸውን ድርጅቶች ባወጣው ጨራታ መሠረት ሲያወዳድር ቆይቷል፡፡
ከተወዳዳሪዎች መካከልም መልቲ ቾይዝ ኢትዮጵያ ባቀረበው የቴክኒክ እና የገንዘብ ንድፈ ሀሳብ (ፕሮፖዛል) የተሻለ ሆኖ በመገኘቱ በቀጣይ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድርን በዲ ኤስ ቲቪ ለማስተላለፍ ተመራጭ መሆኑን የስፖርት ኮሚሽን ገልጿል፡፡
ድርጅቱ ውድድሩን በቀጥታ ለማስተላለፍ እና ለውድድር ስያሜ ለ 5 ዓመት 22.5 ሚሊዮን ዶላር ያቀረበ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ ለስልጠና እና አቅም ግንባታ ፣ ለፕሮዳክሽን ፣ ለአየር ስዓት ወጪ እና ለአይሲቲ መሠረተ ልማት ግንባታ ከ45.5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ እንደሚያደርግ ታውቋል፡፡
በአጠቃላይ በአምስት ዓመት ውስጥ ከ68 ሚሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስት ለማድረግ በተስማማው መሠርት መልቲ ቾይዝ ኢትዮጵያ አሸናፊ ሊሆን ችሏል፡፡
በተለይም ድርጅቱ የሀገሪቱን የስፖርት ደረጃ ለማሻሻል በታዳጊ ወጣቶች ፣ የዳኞች እና አሠልጣኞች አቅም ግንባታ ፣ የስታዲም አካባቢ ፀጥታ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት እንዳለው የኮሚሽኑ መረጃ ያመለክታል፡፡
ድርጅቱ በቀጣይ ጥቂት ቀናት ውስጥ ከሊግ ካምፓኒው ጋር የውል ስምምነት በማድረግ ወደ ስራ እንደሚገባ ሊግ ካምፓኒው አስታውቋል ፡፡
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ታህሳስ 03/2013 ዓ.ም እንደሚጀመር ኮሚሽኑ ትናንት መስከረም 26 ይፋ ማድረጉ ይታወቃል፡፡