ስፖርተኞች ቤታቸው እንዲቀመጡ ሲገደዱ ለስነልቦናዊ ችግር እንደሚጋለጡ የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ
በኢትዮጵያ ስፖርተኞች ጊዜያቸውን እንዴት እያሳለፉ ነው?
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በመላው ዓለም በሚካሄዱ ስፖርታዊ ዉድድሮችና እንቅስቃሴዎች ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አሳድሯል፡፡
በቫይረሱ ምክንያት እግርኳስን ጨምሮ ስፖርታዊ ዉድድሮች እና ልምምዶች በመቋረጣቸው ስፖርተኞች በቤታቸው ለመቀመጥ ተገደዋል፡፡ በተለይ ደግሞ በርካታ ተከታታዮች ያሉት ተወዳጁ የእግር ኳስ ስፖርት ኮቪድ-19 ጠባሳውን ያሳረፈበት ዋነኛው ዘርፍ ነው፡፡
በኢትዮጵያም በየትኛውም ሊግ የሚካሄዱ ዉድድሮች ከተቋረጡ ሰነባብተዋል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከሳምንት በፊት ባወጣው መግለጫ፣ የ2012 ሁሉም የሊግ ውድድሮች እንዲሰረዙ ዉሳኔ ማሳለፉ ደግሞ ግማሽ ያክል ዉድድሮች የሚቀሩት ስፖርቱ በያዝነው ዓመት ፍሬ አልባ ሆኖ እንዲቋጭ ግድ ብሏል፤ ሻምፒዮንም ወራጅም የለም፡፡ የተጫዋቾች ልፋትና ክለቦች ያፈሰሱት ገንዘብም መና ቀርቷል፡፡
ይህ እንዳለ ሆኖ ቀጣይ ውድድር እስኪጀመር ስፖርተኞች፣ በተለይም እግር ኳስ ተጫዋቾች ጊዜያቸውን እንዴት ያሳልፋሉ የሚለው አንዱ ዋነኛ ጥያቄ ነው፡፡
ይህ ወቅት በመላው ዓለም ለሚገኙ ስፖርተኞች እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡ ሜዳ ላይ ልምምድ መስራት እና መቧረቅ የለመዱ ስፖርተኞች ቤታቸው እንዲቀመጡ ሲገደዱ ለከፍተኛ ስነልቦናዊ እና ስነ-አካላዊ ችግር እንደሚጋለጡ የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ ተጽእኖው በእግር ኳስ ተጫዋቾች ላይ ደግሞ ይበልጥ እንደሚበረታ የማንችስተር ዩናይትድ ክለብ የቀድሞ ሳይኮሎጂስት ቢል ቤስዊክ፣ በኮሮና ምክንያት ዉድድሮች ከመቋረጣቸው ጋር በተያያዘ በሰጡት ሙያዊ አስተያየት፣ ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም እግር ኳስ ተጫዋቾች በቤት ዉስጥ በግልም ይሁን ከቤተሰብ ጋር የተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ቢያደርጉ ወደ ዉድድር በሚመለሱበት ወቅት እንዳይቸገሩ ይረዳቸዋል፡፡ ወትሮውንም በታታሪነቱ የሚታወቀው የቅዱስ ጊዮርጊሱ ተጫዋች አብዱልከሪም መሀመድ በዚሁ ጉዳይ ለአል ዐይን አማርኛ ሀሳቡን እና ልምዱን አካፍሏል፡፡
ተጫዋቹ በአሁኑ ጊዜ፣ ሊጉ ከተቋረጠ በኋላ ከካምፕ ወጥቶ፣ በሲዳማ ዞን ወንዶ ገነት ከቤተሰቡ ጋር ጊዜውን በማሳለፍ ላይ ይገኛል፡፡ ባለበት ሆኖ ታዲያ የተለመደውን ስፖርታዊ እንቅስቃሴውን ከማድረግ አልተቆጠበም፡፡ ጊቢዉን ለስፖርት አመቺ በሆነ መልኩ አሰናድቶ፣ አስፈላጊ ቁሳቁሶችን በማሟላት በየእለቱ ስፖርት መስራቱን ቀጥሏል፡፡
ሜዳ ላይ ካለው ጽናት እና ፍጥነቱን እንደጠበቀ ሙሉ ጨዋታውን ያለድካም ከማድረጉ ጋር በተያያዘ “ተርሚኔተር” በሚል ቅጽል ስሙም የሚታወቀው አብዱልከሪም ለብዙ ተጫዋቾች ተምሳሌት እንደሚሆን የቡድን አጋሮቹም ይመሰክራሉ፡፡
ተጫዋቹ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር በስልክ ባደረገው ቆይታ ተጫዋቾች በቤታቸው በሚገኙበት በዚህ ጊዜ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ጤናቸውን ከመጠበቅ ባለፈ ለቀጣይ የዉድድር ጊዜ በአካል እና በስነልቦና ዝግጁ እንዲሆኑ መልእክቱን አስተላልፏል፡፡ ከስፖርት ባለፈ ቤት ዉስጥ ከቤተሰባቸው ጋር የተለያዩ ስራዎችን ቢሰሩ ስነልቦናዊ ደህንነታቸውን ሊጠብቁ እንደሚችሉም የራሱን ተሞክሮ በማንሳት ይመክራል፡፡
በበጎ አድራጎት ስራም ላይ ተሳትፎ በማድረግ ላይ የሚገኘው አብዱልከሪም መሀመድ ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ከ3 ሳምንታት በፊት በትውልድ ስፍራው ወንዶ ገነት ከፍተኛ ገንዘብ ወጪ በማድረግ ፈሳሽ ሳሙና፣ ሳኒታይዘር እና ለእጅ መታጠቢያነት የሚያገለግሉ የዉሃ ሮቶዎችን አድሏል፡፡
አብዱልከሪም አሁን ከሚጫወትበት የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ በተጨማሪ በክለብ ደረጃ ለኢትዮጵያ ቡና፣ ሲዳማ ቡና እና ሀዋሳ ከነማ ክለቦች በፕሮፌሽናል ተጫዋችነት ማገልገሉ ይታወቃል፡፡
ተጫዋቹ ካሸነፋቸው ሽልማቶች መካከል በ2010 ዓ.ም የውድድር ዘመን በምርጥ ተጫዋችነት ዘርፍ ያሸነፈው የኢቢሲ አዋርድ እንዲሁም በዚያው ዓመት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የዓመቱ የፕሪሚየር ሊጉ ምርጥ ተጫዋችነት ሽልማቶች ይጠቀሳሉ፡፡