በየትኛውም ሊግ የ2012 ሻምፒዮን እንዲሁም ወራጅ እንደማይኖር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ገልጸ
በየትኛውም ሊግ የ2012 ሻምፒዮን እንዲሁም ወራጅ እንደማይኖር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ገልጸ
የ2012 ሁሉም የሊግ ውድድር መሰረዙን ፌዴሬሽኑ ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ፡፡
የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በ2012 ሲካሄዱ በነበሩ አጠቃላይ የሊግ ውድድሮች እጣ ፈንታ ላይ በዛሬው እለት በቴሌ ኮንፈረንስ እና በአካል በፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ነው ሁሉም ዉድድሮች እንዲሰረዙ ውሳኔ ያሳለፈው።
በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የተቋረጡ የሊግ ውድድሮች ቀጣይ እጣ ፈንታ ላይ ውይይት ያደረገው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከዚህ ቀደም ከመንግስት ጋር ዛሬ ደግሞ ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አብይ ኮሚቴ ጋር በጉዳዩ ላይ እንደመከረ በድረ ገጹ ባወጣው መግለጫ ይፋ አድርጓል፡፡
በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ መሆኗን ከግምት በማስገባት እንዲሁም ወረርሽኙን መቼ መቆጣጠር እንደሚቻል ማወቅ አስቸጋሪ በመሆኑ ቀጣይ ውድድሮች መቼ እንደሚደረጉ ማወቅ ስለማይቻል ውሳኔው መተላለፉን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ገልጿል፡፡
በውሳኔው መሰረት የ2012 ሁሉም የሊግ ውድድሮች ሙሉ በሙሉ ተሰርዘዋል፡፡ ውድድሩ በመሰረዙም በየትኛውም ሊግ ሻምፒዮን እንዲሁም ወራጅ የሌለ በመሆኑ ቀጣይ ዓመት በአፍሪካ ሻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌዴሬሽን ካፕ ኢትዮጵያን የሚወክል ክለብ አይኖርም ተብሏል።
በ2012 ሰኔ 30 ኮንትራታቸው የሚጠናቀቅ ተጫዋቾች፣ የኮንትራት ጊዜያቸው እስከሚጠናቀቅ ድረስ ክለቦች ኮንትራታቸውን እንዲያከብሩ መወሰኑንም ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።