የብሔራዊ ደህንነትን በሚፈታተኑ ኃይሎች ላይ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ መጀመሩን የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ
ጉሙዝ ታጣቂዎችን በማሰልጠንና አስታጥቀው በማሰማራት ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየተሰራ መሆኑንም ገልጿል
ሀገራዊ ትርምስ ለመፍጠር የተዘጋጁ ሰነዶችና የጥፋቱን ተዋናዮች የሚገልፅ መረጃ በደህንነትና በጸጥታ መዋቅሩ እጅ መግባቱ ተጠቁሟል
መንግስት ሀገራዊ ለውጡ እንዳይቀለበስ እንዲሁም የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት ካለው ፅኑ ፍላጎት አኳያ እያሳያ ያለውን ሆደ ሰፊነትና ታጋሽነት ብሄራዊ ደህንነትን የሚፈታተን በመሆኑ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ መጀመሩን የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል አስታውቋል።
ከሀገር መከላከያ ሚኒስቴር፤ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፤ ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንና ከኢንፎርሜሽን መረብና ደህንነት ኤጀንሲ የተውጣጣው የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል ባወጣው መግለጫ ፣ መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስጠበቅ እያካሄደ ባለው የህግ ማስከበር ዘመቻ በጽንፈኞቹ የህወሓትና የኦነግ-ሸኔ ቡድኖች እንዲሁም በሌሎች ታጣቂዎች ላይም ህጋዊ እርምጃ እየወሰደ ይገኛል ብሏል፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በታለመለት ጊዜ ለማካሄድና በመጀመሪያው ዙሩ ሁለቱ ተርባይኖች ኃይል ማመንጨት እንዲጀምሩ መንግስት በከፍተኛ ትኩረት እየሰራ ነው፡፡
ይሁንና እነዚህ አዎንታዊ ተግባሮች እየተከናወኑ ባሉበት በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱን ወደ ግጭትና ትርምስ ውስጥ ለመክተት ህዝባዊ እምቢተኝነት እንዲፈጥር የውስጥና የውጭ ሃይሎች ተጣምረው የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እያደረጉ መሆኑ በበቂ መረጃና ማስረጃ መረጋገጡን ከደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል የተሰጠ መግለጫ አመልክቷል፡፡
ሀገራዊ ትርምስ ለመፍጠር የተዘጋጁ ሰነዶችና የጥፋቱን ተዋናይ አካላትንም የሚገልፅ መረጃ በደህንነትና በጸጥታ መዋቅሩ እጅ መግባቱንም ተጠቁሟል፡፡
መንግስት መጪው ሀገራዊ ምርጫ ነጻ፣ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ካለው ፅኑ ፍላጎትና ከተጣለበት ሀገራዊ ሃላፊነት የተነሳ የጽንፈኛ ሃይሎችን ተግባር በሆደ ሰፊነትና በትዕግስት ሲከታተልና በአንዳንዶቹም ላይ የእርምት እርምጃ ሲወስድ መቆየቶን ያመለከተው መግለጫው፤ ይሁንና እነዚህ ፅንፈኛ ሀይሎች በማህበራዊ ሚዲያው የሚታየውን ልቅነት ለእኩይ ሴራቸው በቅስቀሳ መሳሪያነት በመጠቀምና የእነሱ ግብረ አበሮች ከሆኑ የጥፋት ሀይሎች ጋር በመቀናጀት ሰሞኑን በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች በንፁሃን ዜጎች ላይ ሞትና መፈናቀል ፈፅመዋል፡፡ ይህም መላውን የሀገራችንን ህዝቦች አሳዝኗል፤ አስቆጥቷልም፡፡ መንግስትንም በእጅጉ አሳዝኗል፡፡
ሰሞኑን በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋና በኦሮሞ ብሔረስብ አስተዳደር ዞኖች ከውስጥና ከውጭ የተደራጁ የጥፋት ሃይሎች በፈፀሙት ጥቃት ንጹኃን ዜጎች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ንብረት ወድሟል ፤ እንዲሁም በርካታ ሰዎች ከቀዬቻው ተፈናቅለዋል፡፡ በዚሁ ክልል በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የቅማንት ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃትም የፀጥታ አካላትን ጨምሮ የንፁሃን ዜጎች ህይወት አልፏል፡፡ ንብረትም ወድሟል፡፡ በሌላም መልኩ በአፋርና በሱማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የንፁሃንን ሕይወት የቀጠፉ ግጭቶች አጋጥመዋል፡፡
በተመሳሳይ በቅንጅት የሚሰሩት የውስጥና የውጭ ጸረ ሰላም ሀይሎች የህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በታለመለት ጊዜ እንዳይካሄድና እንዲስተጓጓል ለማድረግ የጉሙዝ ታጣቂዎችን አሰልጥነውና አስታጥቀው በአካባቢው በማሰማራት ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሰሩ ቢሆንም ድርጊታቸው ከመንግስት እውቅና ውጭ ባለመሆኑ ሴራቸውን ለማክሸፍ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የደህንነትና የፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይሉ ገልጿል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ፀጥታን ለማስከበር እየተወሰደ ባለው እርምጃም ከፍተኛ ኪሳራ እየደረሰበት ያለው የኦነግ-ሸኔ ታጣቂ ቡድን የመንግስትን ትኩረት ለመበተን በማለም በተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚፈፅማቸውን ጥቃቶችና ግድያዎች ሙሉ በሙሉ ለማስቆም በቡድኑ ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃም ተጠናክሮ መቀጠሉን የጋራ ግብረ ሃይሉ በመግለጫው አስታውቋል፡፡
የውስጥና የውጭ ሀይሎች ኢትዮጵያን የማፍረስ ሴራቸውን ለማሳካት በሀገር ውስጥና በውጭ ያሉ የማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎችን እንዲሁም በዚሁ እኩይ ኣላማቸው የተጠለፉ በመንግስት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ አካላትንም ጭምር በመጠቀም፤ ንጹሃንን በግፍ እየገደሉና እያፈናቀሉ ህዝባዊ ቁጣ እንዲቀሰቀስ በማድረግ የሀገርን ህልውና እንዲሁም የዜጎችን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ ለመጣል እየተረባረቡ መሆኑን መላው ህዝባችን ሊገነዘብ ይገባዋልም ነው ያለው፡፡
መንግስት ሀገራዊ ለውጡ እንዳይቀለበስ እንዲሁም የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት ካለው ፅኑ ፍላጎት አኳያ እያሳያ ያለውን ሆደ ሰፊነትና ታጋሽነት ብሄራዊ ደህንነትን የሚፈታተን በመሆኑ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ መጀመሩን የጋራ ግብረ ሃይሉ አስታውቋል።
መንግስት ሀገራዊ ህልውናን አደጋ ላይ ለመጣል የሚሞክሩ የውስጥና የውጭ ፀረ ሰላም ኃይሎችን በምንም አይነት ሁኔታ የማይታገስ በመሆኑ በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍሎች የሚካሄዱ የፀረ ሰላም ኃይል ታጣቂዎችን እንቅስቃሴ በመረጃ፣ በደህንነትና የፀጥታ መዋቅሩ አማካኝነት በመከታተልና በመቆጣጠር፣ አፋጣኝ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ እንደሚገኝ የገለጸው ግብረ ኃይሉ፤ የሀገሪቱን ሰላምና ፀጥታ በአስተማማኝ ደረጃ ላይ ለማድረስ፣ እየተወሰደ ያለው መጠነ ሰፊ ህግን የማስከበር እርምጃ ስኬታማ እንዲሆን፤ ህብረተሰቡ የጥፋት ሀይሎችን ለመቆጣጠር በሚደረገው እንቅስቃሴ ጥቆማ በመስጠትና በማጋለጥ እንዲተባበር የጋራ ግብረ ኃይሉ ጠይቋል።