የቀድሞ የእግር ኳስ ተጫዋችና ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ (ሊብሮ) ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ
ገነነ መኩሪያ ባደረበት ህመም ምክንያት በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ዛሬ ንጋት ላይ ህይወቱ አልፏል
ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ በበርካቶች ዘንድ"ተንቀሳቃሹ ቤተ መፅሐፍት"የሚል ቅፅል ተሰጥቶታል
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ በተጫዋችነት፣ ጋዜጠኝነት እና በመፅሐፍ ደራሲነት ለረጅም ዓመታት ያገለገለው ጋዜጠኛ ገነነ መኩርያ (ሊብሮ) ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።
ጋዜጠኛ ገነነ መኩርያ (ሊብሮ) ባደረበት ህመም ምክንያት በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ህይወቱ ዛሬ ጥር 14 ቀን 2016 ዓ.ም ንጋት ላይ ህይወቱ ማለፉ ተሰምቷል።
ገነነ መኩርያ (ሊብሮ) በእግር ኳስ ተጫዋችነት ኢትዮ ኤሌክትሪክን ጨምሮ ለሌሎች ክለቦችም ተጫውቷል።
ከተጫዋችነት ከተገለለ በኋላ ከ30 ዓመታት በላይ በስፖርት ጋዜጠኝነት ማሳለፉን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መረጃ ያመለክታል።
በበርካቶች ዘንድ"ተንቀሳቃሹ ቤተ መፅሐፍት"የሚል ቅፅል ስም የተሰጠው ገነነ መኩርያ ኢህአፓና ስፖርት"1፣ 2፣ 3፣ ሊብሮ፣ እና ፍትሃዊ የጠጅ ክፍፍል የሚሉተን ጨምሮ ስምንት ያህል መፅሐፍትንም ለንባብ አብቅቷል።
ገነነ መኩርያ ሊብሮ” የተሰኘ ጋዜጣንም ለረጅም ዓመታት ለአንባቢው አድርሷል። በተጨማሪም በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያው በዛሚ ኤፍ ኤም ስፖርትና የቀድሞ ሙዚቃዎችን ታሪክ፣ በኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ከአዲስ ዜማ፣ በብስራት ኤፍ ኤም “መሴ ሪዞርት” እና ሌሎች ዝግጅቶች ላይ ታሪክና ስፖርትን አዋህዶ ሲያቀርብ ቆይቷል።
ገነነ መኩርያ (ሊብሮ) ለእግር ኳሱ ላበረከተው የላቀ አስተዋፅኦም በአዲስ አበባ በተሰናዳው የካፍ ኮንግረስ ላይ የረጅም ዘመን አግልግሎት ሜዳይ ተበርክቶለታል።
ካፍ በ2009 ዓ.ም የ60 ዓመት ጎንደል ኦፍ ሜሪት የሸለመው ሲሆን፤ ስድስት ጋዜጠኞች ብቻ ያገኙትን ሽልማት በመውሰድ ገነነ ከምስራቅ አፍሪካ ብቸኛው እንደሆነም ይነገራል።
ጋዜጠኛው መጋቢት 5 ወን 1957 ዓ.ም በይርጋለም ከተማ እንደተወለደ ሲሆን፤ እድገቱ ደግሞ በሻሸመኔ ከተማ እንደሆነ የህይወት ታሪኩ ይናገራል።