የኢትዮጵያ እና ሱዳን ባለስልጣናት የድንበር ግጭትን ለመከላከል መከሩ
በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል ያለው ድንበር ባለመካለሉ ምክንያት ግጭት ሲነሳ ቆይቷል
በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል ያለውን ግጭት ለመከላከል የሁለቱ ሀገራት ባለስልጣናት በባህርዳር መክረዋል
በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል ያለውን ግጭት ለመከላከል የሁለቱ ሀገራት ባለስልጣናት በባህርዳር መክረዋል
የኢትዮጵያና የሱዳን ባለስልጣናት በሁለቱ ሀገራት ድንበር ላይ ሲስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን በመፍታት ሰላም ለማስፈን በሚስሩበት ሁኔታ ላይ በባህርዳር መወያየታቸውን የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት/አብመድ/ ዘግቧል፡፡
ውይይታቸው በሁለቱ ሀገራት ድንበር ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመከላከል እንደሚረዳ ዘገባው ጠቅሷል፡፡
በኢትዮጵያ በኩል ብርጋዴር ጄኔራል ሙሉዓለም አድማሱ እና ሱዳኑ በኩል ሜጀር ጄኔራል ሷልህ አብደላ ኢሳቅ በድንበር አካባቢ ያለውን ሰላም ለማስፈን በሚሰሩበት ሁኔታ ላይ በባህርዳር በነበራቸው ውይይት ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ሱዳን መካከል ያለው ድንበር እስካሁን ባለመከለሉ ምክንያት በተለያ ጊዜ ግጭት ይነሳል፤ ግጭቱም በርካታ ሰዎች ይገደላሉ፡፡ ከ 4 ወራት በፊት በሁለቱ ሀገራት በሰሜን ምእራብ ወይም በአማራ ክልል በኩል ባለው ድንበር ላይ በተነሳው ግጭት የሰዎች ሕይወት አልፏል፡
ሱዳን ወታደሮቿ በኢትዮጵያ ወታደሮች በሚታገዙ ታጣቂዎች እንደተገደሉባት ከሳ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ለዚህ ክስ በወቅቱ መልስ አልሰጠችም ነበር፡፡
ከግጭቱ በኋላ ኢትዮጵያና የሱዳን ባለስልጣናት በመገናኘታቸው ጉዳዩ በዲፕሎማሲ መፈታቱ የሚታወስ ነው፡፡
የሱዳን ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሀምዶክ ከሱዳን ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ሀገራቸው ከጎረቤት ኢትዮጵያ ጋር ጸብ የመፍጠር ዓላማ የላትም ማለታቸው ይታወሳል፡፡
ግጭቱ በተከሰተ ሰሞን ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ቆይታ አድርገው የነበሩት ቀድሞው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን “ከሱዳን ጋር በተያያዘ ከሰሞኑ ሲናፈሱ የሰነበቱት ጉዳዮች የግድቡን አጀንዳ ወደ ድንበር አጀንዳነት ለማምጣት በማሰብ የተደረጉ” መሆናቸውን ገልጸው ነበር፡፡