ኢትዮጵያ እና ሱዳን የድንበር እና የግድቡን ጉዳዮች በንግግር ብቻ ለመፍታት ተስማሙ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሱዳን ያደረጉት የአንድ ቀን ጉብኝት ስኬታማ መሆኑን ገልጸዋል
በቀጣዩ ወር የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር በኢትዮጵያ ተገኝተው የህዳሴ ግድቡን እንደሚጎበኙ ይጠበቃል
ኢትዮጵያ እና ሱዳን የድንበር እና የግድቡን ጉዳዮች በንግግር ብቻ ለመፍታት ተስማሙ
በኢትዮጵያ እና ሱዳን የሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ በካርቱም የተወያዩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሱዳኑ አቻቸው አብደላ ሃምዶክ የጋራ ሰላም እና ጸጥታ ፣ ዲሞክራሲ እና የኢኮኖሚ እድገትን ለማረጋገጥ በትብብር ለመስራት ተስማምተዋል፡፡
ዉይይታቸው መጠናቀቁን ተከትሎ የሁለቱን ሀገራት የጋራ አቋም እና መሪዎቹ የደረሱበትን ስምምነት የሚያንጸባርቅ መግለጫ አውጥተዋል፡፡
በሁለቱም ሀገራት የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ በትብብር መስራት ከተቻለ ለቀጣናው የብርሀን ጮራ የሚፈነጥቅ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከውይይቱ በኋላ ተናግረዋል፡፡
የሁለቱ ሀገራት ታሪካዊ ፣ ባህላዊ ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ቀጣናዊ ትስስርን መፍጠሪያ መሳሪያ በመሆን የሁለቱን ወንድማማች ህዝቦች የሰላም ፣ የብልጽግና እና የፓን አፍሪካኒዝም ምኞት ለማሳካት እንደሚያስችል የገለጹት ደግሞ ጠ/ሚ ሃምዶክ ናቸው፡፡
ሱዳን ዉስጣዊ ችግሮቿን በዉይይት ለመፍታት የምትወስዳቸውን እርምጃዎች ኢትዮጵያ ያደነቀች ሲሆን ሁለቱ ሀገራት የቆዩ የጋራ ችግር መፍቻ ዘዴዎችን በመጠቀም በመካከላቸው ያሉ የድንበር እና ከሕዳሴ ግድብ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችንም በውይይት ብቻ ለመፍታት ተስማምተዋል፡፡
ከአሜሪካ ‘ሽብርተኝነትን የሚደግፉ ሀገራት ዝርዝር መዝገብ’ ዉስጥ የሱዳን ስም እንዲሰረዝ ኢትዮጵያ ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አረጋግጠዋል፡፡ ሀገሪቱ ከገባችበት የኢኮኖሚ ቀውስ አንጻር የዕዳ እፎይታ እና ስረዛ እንዲደረግላት ኢትዮጵያ የጀመረችውን ጥረት እንደምትቀጥልም እንዲሁ፡፡
በአፍሪካ ቀንድ የሰፈነው አንጻራዊ ሰላም እና መረጋጋት ዘላቂነት እንዲኖረው ሱዳን እና ኢትዮጵያ በቀጣናዊ ጉዳይ የጀመሯቸውን የጋራ ተግባራት ይበልጥ ሊያሳድጉ እንደሚገባም ተወያይተዋል፡፡
የህዳሴ ግድቡን በተመለከተ በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት የሚከናወነው የሶስትዮሽ ድርድር ዉጤታማ እንዲሆን በመተማመን ላይ የተመሰረተው ዉይይት እንዲቀጥል ሁለቱ ጠቅላይ ሚኒስትሮች እና ካቢኔዎቻቸው ተስማምተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ በቀጣዩ ወር ለጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ ሊመጡ እንደሚችሉ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ፣ “የጋራ ፕሮጄክታችን የሆነውን የህዳሴውን ግድብ በአንድነት ልንጎበኝ እንችላለን” ብለዋል፡፡
በዓባይ ጉዳይ ላይ ሁሉም ተጠቃሚ የሚሆኑበት እና በተፋሰሱ ሀገራት መካከል ትብብርን የሚፈጥር ስምምነት ሊደረስ እንደሚገባም መሪዎቹ አቋማቸውን አንጸባርቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና ልዑካቸው ከሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ፕሬዝደንት ጄኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሃን ጋርም ተወያይተዋል፡፡