ኢትዮጵያ የ2020 የቶኪዮ ኦሎምፒክ ላይ በ4 አይነት የስፖርት አይነቶች ትሳተፋለች
በቶኪዮ 2020 ኢትዮጵያን የሚወክለው የአትሌቲክስ ቡድን ሁለተኛው ዙር ተጓዥ ወደ ጃፓን አመራ።
ለአትሌቲክስ ቡድኑ በትላንትናው እለት ምሽት ሽኝት እንደተደረገለትም የኢትዮጵያ ስፖርት ኮሚሽን በፌስቡክ ገጹ አስነብቧል።
ተጓዦችን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀብታሙ ሲሳይ በቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በመገኘት አሸኛኘት አድርገውላቸዋል።
ወደ ጃፓን ከተጓዙ የአትሌቶች ብድን ውስጥም 3000 ሜትር መሰናክል ወንዶች አትሌት ታደሰ ታከለ፣ አትሌት አብርሀም ስሜ፣ አትሌት ኃ/ማርያም አማረ እና አትሌት ጌትነት ዋለ እንደሚገኙበት ከኢትጵያ አትሌቲክስ ፍዴሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
እንዲሁም 5000 ሜትር ሴቶች አትሌት እጅጋየሁ ታዬ፤ 800 ሜትር ሴቶች አትሌት ወርቅነሽ መለሰ እንደሚገኙበትም ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።
በጃፓን አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው 32ኛው የ2020 የቶክዮ ኦሎምፒክ ባሳለፍነው አርብ በይፋ መጀመሩ ይታወሳል።
ኢትዮጵያ የ2020 የቶኪዮ ኦሎምፒክ ላይ በ4 አይነት የስፖርት አይነቶች ማለትም በአትሌቲክስ፣ ብስክሌት፣ ውኃ ዋናና ከቴኳንዶ ትሳተፋለች።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያነ በመወከል ወደ ቶኪዮ ኦሊምፒክ የሚጓዙት አትሌቶችና አሰልጣኞች 65 መሆናቸውም ይታወቃል።
በድምሩ ኢትዮጵያን በመወከል ወደ ጃፓን የሚያመራው ልዑክ ከ90 በላይ አባላት የያዘ መሆኑንም የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ለአል ዐይን መግለጹ ይታወሳል።
በዘንድሮው የ2020 የቶኪዮ ኦሎምፒክ ላይ ከ205 ሀገራት የተውጣቱ ከ11 ሺህ በላይ አትሌቶች እንደሚሳተፉ ከስፍራው ተገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በቶኪዮ ኦሎምፒክ ላይ 33 አይነት ስፖርታው ጨዋታዎች የሚካሄዱ ሲሆን፤ በውድድሩ ለሚያሸንፉ አትሌቶችም 5 ሺህ ሜዳሊያዎች ለሽልማት ተዘጋጅተዋል።