ከ50 በመቶ በታች ያመጡ ተማሪዎች በቀጥታ ወደ ዩንቨርስቲ እንደማይገቡ ትምህርት ሚንስቴር አስታወቀ
895 ሺህ 520 ተማሪዎች ተፈትነው 350 እና ከዛ በላይ ውጤት ያመጡት 29 ሺህ 900 ተማሪዎች ብቻ ናቸው
የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ውጤትን ትናንት ተለቋል
ከ50 በመቶ በታች ያመጡ ተማሪዎች ወደ ዩንቨርስቲ በቀጣታ እንደማይገቡ ትምህርት ሚንስቴር አስታወቀ።
የትምህርት ሚንስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ የ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ውጤት ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
እንደ ሚንስትሩ ገለጻ ከሆነ የ2014 ብሔራዊ የ12ኛ ክፍል ፈተናን 895 ሺህ 520 ተማሪዎች ተፈትነው 350 እና ከዛ በላይ ውጤት ያመጡት 3 ነጥብ 3 በመቶ ወይም 29 ሺህ 900 ተማሪዎች ብቻ ናቸው።
ይህ የፈተና አሰጣጥ ሂደት ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን ያነሱት ፕሮፌሰር ብርሀኑ ፈተናዎች ተማሪዎችን በትክክል እየመዘኑ ባለመሆኑ እና ይህ መቆም አለበት በማለት ወደ ዩንቨርስቲዎች ገብተቅ እንዲፈተኑ መደረጉንም ጠቅሰዋል።
በዚህ ፈተና ወቅት በነበሩ የደንብ ጥሰቶች 20 ሺህ 170 ተማሪዎች እንደተቀጡም ሚንስትሩ በመግለጫቸው ላይ ጠቅሰዋል።
በሀገር ደረጃ የተመዘገበ ከፍተኛ ውጤት ከሰባት መቶ 666 (በተፈጥሮ ሳይንስ ) ሲሆን በማህበራዊ ሳይንስ ከስድስት መቶ 524 ከፍተኛቹ ውጤቶች ሆነው መመዝገባቸውም ተገልጿል።
ወንዶች ከሴቶች የተሻለ ውጤት አስመዝግበዋል የተባለ ሲሆን በክልሎች መካከል የተጋነነ ልዩነት ባይኖርም አዲስ አበባ፥ ሀረሪ እና ድሬዳዋ የተሻለ ነጥብ መመዝገቡንም ፕሮፌሰር ብርሀኑ ተናግረዋል።
በጠቅላላው በአማካይ ከ50 በመቶ በላይ ያመጡት ከተፈጥሮ ሳይንስ 22 ሺህ ተማሪዎች ፣ ከማህበራዊ ሳይንስ ደግሞ 6 ሺህ 973 ተማሪዎች ብቻ እንዳለፉ ተጠቅሷል።
ተማሪ ሚኪያስ አዳነ ከደሴ አዳሪ ትምህርት ቤት 666 በማምጣት በሀገር አቀፍ ከፍተኛው ውጤት እንደሆነ ተገልጿል።
ከግማሽ በላይ ውጤት አምጥተዋል ከተባሉት ማለትም ከ29 ሺህ 900 ተማሪዎች ውጭ የተቀሩት ተማሪዎች እጣ ፈንታ ምን ይሆናል? በሚል ለቀረበው ጥያቄም ከ50 በመቶ በታች ያመጣ ማንም ተማሪ በሚቀጥለው አመት ፍሬሽ ማን ሆኖ ወደ ዩኒቨርሲት አይገባም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
በቀጣይ በቀረበው የመፍትሄ አቅጣጫ የተዳከውሙባቸውን ትምህርቶች በዩኒቨርስቲ ዳግም እንዲማሩ ተደርጎ በአመቱ መጨረሻ እንዲፈተኑ በማድርረግ ያለፉት የዩንቨርሲቲ ስርዓቱን የሚቀላቀሉ ይሆናል ተብላል።