ድምጻዊው በዛሬው ዕለት ሆስፒታል ውስጥ በህክምና ላይ እያለ ህይወቱ አልፏል
ድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።
የመጀሙሪያ አልበሙን በ1987 ዓ.ም "ስያሜ አጣሁላት" በሚለው የሙዚቃ ስራው ከሙዚቃ አፍቃሪዎች ጋር የተዋወቀው ተወዳጁ ድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ አርፏል።
ድምጻዊው ባደረበት ህመም ምክንያት በዛሬው ዕለት በሆስፒታል ህክምና ላይ እያለ ማረፉን አል ዐይን ከቅርብ የሙያ አጋሮቹ አረጋግጧል።
ድምፆዊ ማዲንጎ አፈወርቅ በሰራቸው ሶስት ዓልበሞች ዘመን የሚሻገር ስራ ባለቤት ነበር።
ኢትዮጵያ በተፈተነችበት ወቅት እያመመው ግንባር ድረስ በመሔድና ማሰልጠኛም ምልምሎችን በማነቃቃት የራሱ የሆነ ታሪክ የሰራ አርቲስት ነበር።
"ስያሜ አጣሁላት" "አይደረግም" እና "ስወድላት" በተሰኙት አልበሞቹ እና በነጠላ ዜማዎቹ የሚታወቀው ድምጻዊ ማዲንጎ በሙዚቃ አፍቃሪዎች ዘንድ አይረሴ ያደርገዋል።
በደብረታቦር እንደተወለደ የሚናገረው ድምጻዊ ማዲንጎ አራተኛ አልበሙን ለአድማጮች ለማድረስ በመስራት ላይ እንደነበርም ሰምተናል።
የድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ቤተሰቦች ለሙዚቃ ተሰጥኦ ያላቸው ሲሆን ታናሽ ወንድሙ ያሬድ አፈወርቅ እና እህቱ ትዕግስት አፈወርቅ ተወዳጅ የሆኑ የሙዚቃ ስራዎችን ሰርተው በሙዚቃ አፍቃሪዎች ዘንድ ተወዳጆች ሆነዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ህልፈት ሀዘናቸውን የገለጹ ሲሆን፤ በማህበራዊ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍም፤ “አርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ በማረፉ የተሰማኝ ኀዘን ከባድ ነው” ብለዋል።
“ለሀገሩ በአጭር እድሜው ብዙ የሠራ ከያኒ ነው፤ ሀገር በተደፈረች ጊዜ ሕመሙን እየቻለ ግንባር ተገኝቶ ሠራዊቱን አጀግኗል፤ ሠልጣኞችን አበርትቷል፤ ነፍሱ በሰላም ትረፍ” ብለዋል።
የድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ህልፈትን ተከትሎ በርካታ ወዳጆቹ እና አድናቂዎቹ በተለያየ መንገድ ሀዘናቸውን እየገለጹ ነው።