አትሌት አባዲ ሀዲስ በተለያዩ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ውድድሮች ኢትዮጵያን በመወከል ይታወቃል
አትሌት አባዲ ሀዲስ አረፈ
በተለያዩ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ውድድሮች ኢትዮጵያን በመወከል የሚታወቀው አትሌት አባዲ ሀዲስ ማረፉን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታወቀ፡፡
አባዲ ባደረበት ህመም ምክንያት በመቀሌ አይደር ሆስፒታል በህክምና ሲረዳ ነበር ያለው ፌዴሬሽኑ ትናንት ጥር 26 ቀን 2012 ዓ.ም. ምሽት ላይ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱን ገልጿል፡፡
አትሌቱ በትግራይ ክልል ማይጨው ከተማ ልዩ ስሙ እንዳመሆኒ ወረዳ ነበር ጥር 27 1990 ዓ.ም የተወለደ ሲሆን የአትሌቲክሰ ህይወቱን በእንዳመሆኒ የአትሌቲክሰ ማሰልጠኛ ጣቢያ ነው የጀመረው፡፡
በመቀጠልም በማይጨው አትሌቲክሰ ማሰልጠኛ ማዕከል ገብቶ መደበኛ ስልጠናውን ሲያጠናቅቅ ትራንስ ኢትዮጵያ አትሌቲክሰ ክለብን በመቀላቀል ህይወቱ እስካለፈበት እለት ድረስ በውጤታማነት ክለቡን፣ ክልሉንና ሃገሩ ሲያስጠራ ነበረ፡፡
በ2016 በተካሄደ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የ10 ሺህ ሜትር ውድድር 28፡43.2 በሆነ ሰዓት 1ኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀው አትሌት አባዲ በተለያዩ ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ የውድድር መድረኮች ተሳትፏል፤ ድሎችንም አስመዝግቧል፡፡
ብራዚል ሪዮ ዴ ጄኔሮ በተካሄደው የ2016ቱ የኦሎምፒክ ጨዋታዎች በ10 ሺህ ሜትር በ27፡36.34 በሆነ ሰዓት 15ኛ ደረጃ በመያዝ አጠናቋል፡፡
በዶካ ኳታር በተካሄደው የ2019 የዓለም አትሌቲክሰ ሻምፒዮና በ5 ሺህ ሜትር ውድድር የተሳተፈ ሲሆን በ2017 እንግሊዝ ሎንደን ላይ በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ10 ሺህ ሜትር 26፡59.19 በሆነ ሰዓት 7ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል፡፡
በ2017 ኡጋንዳ ካምፓላ በተካሄደው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በአዋቂ ወንዶች 10ኪ.ሜ. ውድድር በ28፡43 በሆነ ሰዓት 3ኛ ደረጃ በመያዝ የነሃስ ሜዳልያ አሸናፊ ነበረ፡፡
በሞሮኮ ራባት በተካሄደው የ2019 የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ውድድርም በ10 ሺህ ሜትር በ28፡27.38 7ኛ ደረጃ ይዞ ነው ያጠናቀቀው፡፡
የአትሌቱ የቀብር ስነ ስርዓት በነገው እለት የፌዴራልና የክልል አትሌቲክሰ ፌዴሬሽን አመራሮች እና የክለቡ ኃላፊዎች ወዳጅ ዘመዶቹ በተገኙበት በትውልድ ስፍራው እንደሚፈጸም ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡