የድምጻዊ ዳዊት ነጋ የቀብር ስነስርዓት ተፈፀመ
ድምጻዊው በትግሬኛ ዘፈኖቹ ታዋቂነትን አትርፏል
ድምጻዊ ዳዊት በተወለደ 34 ዓመቱ በድንገተኛ ህመም ህይወቱ ማለፉ ይታወሳል
የአንድ ልጅ አባት የነበረው ድምጻዊ ዳዊት 'ባባ ኢለን' የሚለው ሙዚቃው የመጀመሪያ ስራው ነበር
የድምጻዊ ዳዊት ነጋ የቀብር ስነስርዓት በዛሬ እለት በአዲስ አበባ ተፈጽሟል።
የድምጻዊ ዳዊት ነጋ ስርዓተ ቀብር ወዳጅ ዘመዶቹ ፤ አድናቂዎቹ በተገኙበት በአዲስ አበበ መንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን ዛሬ ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም ተፈፅሟል፡፡
ድምጻዊው ከትናንት በስቲያ በአዲስ አበባ ድንገተኛ ህመም ገጥሞት በአዲስ ህይወት ሆስፒታል በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ሰኔ 05 ቀን 2014 ዓ.ም በተወለደ በ34 አመቱ ከዚህ አለም በሞት መለየቱ ይታወሳል
ድምጻዊ ዳዊት የአንድ ልጅ አባት እንደነበር በስርዓተ ቀብሩ ላይ የተነበበው የህይወት ታሪክ ያስረዳል፡፡
የዛሬ 34 አመት በመቐለ እደ ማርያም ሰፈር የተወለደው ድምጻዊ ዳዊት በትግርኛ ሙዚቃ ስራዎቹ አድናቆትን አትርፏል፡፡
ወላጆቹን በህጻንነቱ እንዳጣ የተገለጸው ድምጻዊ ዳዊት የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ በመቀሌ አይደር ትምህርት ቤት ራሱን እንዳስተማረ በሕይወት ታሪኩ ላይ ተጠቅሷል፡፡
ከልጅነቱ አንስቶ ለሙዚቃ ልዩ ፍላጎት እንዳለው የሚነገርለት ድምጻዊ ዳዊት ባባ ኢለን የተባለው የመጀመሪያ የሙዚቃ ስራው ከህዝብ ጋር አስተዋውቆታል ተብሏል፡፡
ዘዊደሮ፣ ወዛመይ፣ ቸኮላታ፣ ኣጆኺ ትግራይ፣ ደስ ይበለኒ'ሎ እና ቕዱስ ፀባያ የተሰኙት ዘፈኖቹ በመላው ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ተወዳጅ ስራዎቹ ናቸው፡፡