መንግስት የሴት ተማሪዎች ወሊድ ፈቃድ ረቂቅ መመሪያን እንዲሰርዝ ተጠየቀ
ትምህርት ሚኒስቴር በወሊድ ምክንያት ለ15 ቀናት ከትምህርት የምትቀር ተማሪ ትምህረቷን መቀጠል እንዳትችል የሚያደረግ መመሪያ ማጋጀቱ ይታወሳል
ይህ መመሪያ ህገ መንግስቱን ጭምር የሚጥስ ነው በሚል ተቃውሞ ገጥሞታል
መንግስት የሴት ተማሪዎች ወሊድ ፈቃድ ረቂቅ መመሪያን እንዲሰርዝ ተጠየቀ፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ተማሪዎች ምዘናና የክፍል ዝውውር ረቂቅ መመርያ ማዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡
ሪፖርተር ጋዜጣ ከአንድ ሳምንት በፊት ባወጣው ዘገባ የአጠቃላይ ትምህርት ተማሪ ከ15 ቀናት በላይ በወሊድ ምክንያት ከትምህርቷ የምትቀር ከሆነ በዚያው የትምህርት ዘመን ትምህርቷን መቀጠል እንደማትችል የሚደነግግ ረቂቅ መመሪያ በትምህርት ሚኒስቴር መዘጋጀቱን ገልጿል፡፡
በዚህ ረቂቅ መመሪያ መሰረትም ተማሪዋ ለ15 ተከታታይ ቀናት በወሊድ ምክንያት የምታርፍ ከሆነ ትምህርቷን መቀጠል አትችልም፡፡
ተማሪዋ ለ16 ቀናትና ከዚያ በላይ ለሆኑ ቀናት የምትቀር ከሆነ በዚያ ዓመት ስትከታተል ከነበረው ትምህርት የምትታገድ መሆኑን ያስረዳል፡፡
ሆኖም ተማሪዋ በቀጣዩ ዓመት ትምህርቷን መቀጠል የምትፈልግ ከሆነ፣ ‹‹ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ›› መቀጠል እንደምትችል ይፈቅዳል ሲል በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ይህን ረቂቅ መመሪያ የተቃወመ ሲሆን መመሪያው ትምህርታቸውን ለሚከታተሉ ሴቶች የወሊድ ፈቃድ መብትን በእጅጉ የሚገድብ እንደሆነ ገልጿል፡፡
ይህ ረቂቅ ሕግ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የተደነገጉትን አወንታዊ የድርጊት ድንጋጌዎች የሚንድ ብቻ ሳይሆን የሴቶችን መሠረታዊ የመማር መብቶችም በግልጽ የሚነፍግ ስለሆነ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አቋሙን እንደገና እንዲያጤነው ሲል ጠይቋል፡፡
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው “የባሎች ትምህርት ቤት” ተከፈተ
መንግስት ያዘጋጀውን ረቂቅ ህግ እንዲሰርዝ ወይም እንዲያሻሽል ሁሉም ተቋማት እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ጫና እንዲያደርጉ ሲል ማህበሩ ጥሪ አቅርቧል፡፡
አልዐይን በጉዳዩ ዙሪያ ከትምህርት ሚኒስቴር ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም፡፡
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በ12ኛ ክፍል ውጤት ዙሪያ በሰጡት መግለጫ ላይ የተማሪዎችን ውጤታማነት ለመለካት እና ለማሻሻል ከትምህርት አሰጣጥ ጀምሮ የተለያዩ ማሻሻያዎችን ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል፡፡