ያለምንም የህግ ትምህርት ለ26 ደንበኞቹ ተከራክሮ ያሸነፈው ሀሰተኛ ጠበቃ ተያዘ
ኬንያዊው ወጣት የሞግሼውን የጥብቅና ፈቃድ በመጠቀም በታዋቂ የህግ አማካሪ ድርጅት ሲሰራ ቆይቷል
የኬንያ የህግ ባለሙያዎች ማህበር የደረሰውን ጥቆማ ተከትሎ ባደረገው ምርመራ “ሀሰተኛ ጠበቃው” በቁጥጥር ስር ውሏል
ከህግ ትምህርት ጋር ምንም ሳይተዋወቅ በፍርድ ቤቶች ደንበኞቹን ወክሎ ሲከራከር የቆየው “ሀሰተኛ ጠበቃ” ተያዘ።
ብሪያን ምዌንዳ ጃጊ የተባለው ኬንያዊ ህግ ባያጠናም የ26 ሰዎች ጠበቃ በመሆን በሁሉም አሸናፊ መሆኑ ግን አነጋጋሪ ሆኗል።
ጃጊ በታዋቂው የጠበቆች የቴሌቪዥን ድራማ “ስዩትስ” ምንም የህግ ትምህርት ሳይኖረው በጥብቅና ሙያ ተሰማርቶ ሲተውን የሚታየውን ገጸባህሪ ማይክ ሮስ በገሃዱ አለም ተክቶታል።
ብሪያን ምዌንዳ ጃጊ በከፍተኛ ፍርድ ቤት ሽንጡን ገትሮ ሲከራከርና የ26 ደንበኞቹ ጠበቃ ሆኖ ሁሉንም አሸናፊ ሲያደርግ የኬንያ ዳኞች አልተጠራጠሩም።
የኬንያ የህግ ባለሙያዎች ማህበር የደረሰው ጥቆማ ግን ሀሰተኛው ጠበቃ በቁጥጥር ስር እንዲውል መነሻ ሆኗል።
ማህበሩ የደረሰው ጥቆማ ብሪያን ምዌንዳ ናትዊጋ የተባለ ህጋዊ ጠበቃ በማህበሩ ድረገጽ ላይ የራሱን አካውንት መክፈትና ፈቃዱን ማደስ አለመቻሉን መግለጹ ነው።
በዚህ መነሻ የተደረገው ምርመራም ሀሰተኛው ጠበቃ ብሪያን ምዌንዳ ጃጊ የትክክለኛውንና ስመ ሞግሼውን ጠበቃ ብሪያን ምዌንዳ ናትዊጋ አካውንት ሰብሮ በመግባት ስምና ምስሉን ቀይሮ የጥብቅና ፈቃድ ወረቀት እንዲሰጠው መጠየቁን ያረጋግጣል።
በናይሮቢ የሚገኘው የኬንያ የህግ ባለሙያዎች ማህበር ምንም የህግ ትምህርት ሳይከታተል ጠበቃ ለመምሰልና የሌላ ጠበቃን አካውንት ሰብሮ በመግባት ፈቃድ ለማግኘት ሞክሯል ያለውን ብሪያን ምዌንዳ ጃጊ በቁጥጥር ስር እንዲውል አድርጓል።
ጃጊ ምንም እንኳን በሞግሼው ስም ለመነገድ መሞከሩ ተገቢነት የሌለው ጉዳይ መሆኑ አከራካሪ ባይሆንም የያዛቸውን 26 ጉዳዮች በብቃት ማሸነፉ ግን አጃኢብ አስብሏል ሲል ያስነበበው ኦዲቲ ሴንትራል ነው።