ሚንስቴሩ “ከቀረቡልኝ የማስረጃ ይረጋገጥልን ጥያቄ 40 በመቶ የትምህርት ማስረጃዎች ሀሰተኛ ሆነው አገኘሁ” አለ
ትምህርት ሚንስቴር ከዚህ በኋላ በተጭበረበረ ማስረጃ የሚሰራ ስራ አይኖርም ብሏል
በ2015 ዓመት የሁሉም የፊደራል ሰራተኞች የትምህርት ማስረጃ ትክክለኛነት እንደሚረጋገጥ አስታውቋል
ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት 18 ሽህ የትምህር ማስረጃዎች ትክክለኛ ተፈትሾ 921 (አምስት በመቶዎቹ) ህገ-ወጥ ሆነው እንዳገኛቸው ትምህርት ሚንስቴር አስታወቀ።
ቀጣሪ ተቋማት ለሚንስቴሩ ይረጋገጥልን ብለው ባቀረቡት ጥያቄ ደግሞ 225 የትምህርት ማስረጃዎች ተመርምረው 40 በመቶዎቹ ሀሰተኛ ሆነው መገኘታቸውንም ሚኒስቴሩ ገልጿል።
ትምህርት ሚንስቴር የዘጠኝ ወር ሪፖርቱን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያቀርብ፤ አባላቱ ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ በስፋት መሰራጨት እንዳሳሰበው ተናግረዋል።
ገዙ ምናዬ የተባሉ የምክር ቤት አባል "በአንዳንድ የግል የትምህርት ተቋማት የሚወጡ የሀሰት የትምህርት ማስረጃዎች በስፋት እየተሰራጩ ስለሆነና ይህም በሀገር አሉታዊ ጫና ስላለው እነዚህን ተቋማት እውቅና ከማሳጣት አንፃር ምን እየተሰራ ይገኛል?" ሲሉ ጠይቀዋል።
የትምህርት ማስረጃ ማጣራትን ከራሳችን ጀምረናል ያሉት የትምህርት ሚንስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)፤ በዚህ ዓመት ሁሉም የፊደራል ተቋማት ሰራተኞች ማስረጃ እንደሚጣራ ገልጸዋል።
"በሁሉም የፌደራል ተቋማት የሰራተኞችን ማህደር መመርመር ጀምረናል። ምን ያህሉ እውነተኛ የትምህርት ማስረጃ ይዞ ነው? ምን ያህሉ አይደለም የሚል ምርመራ እያካሄድን ነው፤ ከራሳችን ጀምረን። ማህበረሰቡ ልክ እንደፈተናው [የ12ተኛ ክፍል ፈተና] እንዲያውቅልን የምንፈልገው ከአሁን በኋላ በተጭበረበረ ድግሪ፤ በተጭበረበረ ዲፕሎማ የሚሰራ ስራ አይኖርም የሚለውን ለማሳወቅ ነዉ። በዚህ ዓመት እሱን እንጨርሳለን ብለን እናስባለን" ብለዋል።
ይህን ለማድረግ ችግሩን ያልደበቁት ሚንስትሩ "ችግሩ ግን የሚታወቅ ነው፤ ሀገሩ የደላላ ሆኗል፤ ቀጥተኛ የሆነ የግብይት ስርዓትና ንፁህ የሆነ ስራን ለመስራት በጣም ብዙ ስራ ይቀረናል" በማለት ተናግረዋል።