የሕወሓት ቡድን አስተባባሪዎችን ለህግ የማቅረብ ሂደቱ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ብልጽግና ፓርቲ ወሰነ
ምርጫ 2013 በስኬት እንዲጠናቀቅ ጠንካራ ዝግጅት እንዲደረግም ኮሚቴው ወስኗል
የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የሁለት ቀናት ስብሰባውን አጠናቋል
የሕወሓት ቡድን አስተባባሪዎችን ለህግ የማቅረብ ሂደቱ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ብልጽግና ፓርቲ ወሰነ
የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለሁለት ቀናት በተለያዩ ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሲያካሂድ የነበረውን መደበኛ ስብሰባ ማጠናቀቁን አስታውቋል።
የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብናልፍ አንዷለም እንዳሉት ስብሰባው በሶስት አጀንዳዎች ላይ የተደረገ ሲሆን አጀንዳዎቹም ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ፣ ሀገራዊ እና ዓለምአቀፋዊ ጉዳዮች እንዲሁም የብልፅግና ፓርቲ የምርጫ 2013 ዝግጅትና ቅስቀሳን የተመለከቱ ናቸው።
በዚህም ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ ላይ በደረገው ውይይት፥ አጥፊው የህወሓት ጁንታ ቡድን በሰሜን እዝ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት መፈፀሙን ተከትሎ፤ መንግስት ተገዶ ሀግን ወደ ማስከበር ስራ መግባቱን አስታውሰዋል።
ኤፍቢሲ እንደዘገበው የሕወሓት ቡድን አስተባባሪዎችን ለህግ የማቅረብ ሂደቱ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ በፓርቲው ስራ አስፈፃሚ ስብሰባ አቅጣጫ መቅመጡን አቶ ብናልፍ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
በህግ ማስከበር ሂደቱ የተጎዱ ዜጎች ወደ ቀያቸ እንዲመለሱና እንዲቋቋሙ፣ የወደሙ መሰረተ ልማቶች ቶሎ ተጠግነው ለህዝብ አገልግሎት እንዲሰጡ አንዲሁም የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በፍጥነት መደበኛ አገልግሎት እንዲጀምሩ መወሰኑንም አንስተዋል፡፡
ሀገራዊ እና ዓለማቀፋዊ ጉዳዮችን በተመለከተም ብሄረ መንግስት እና ሀገረ መንግስት በመገንባት ሂደት ውስጥ ፅንፍ የወጡ አስተሳሰቦች እንደሚስተዋሉ የተመለከተው ስራ አስፈፃሚው፤ ይህንን ለማስተካከል ህዝቡ ፖለቲካዊ ንቃት እንዲኖረው መሰራት አንዳለበት መገምገሙን ነው አቶ ብናልፍ የተናገሩት።
ከዓለም ዓቀፋዊ ሁኔታዎች አንፃር በተለይም የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ከማስጠበቅ አኳያ፥ ከአባይ ፖለቲካ ጋር በተያያዘ የህዳሴ ግድብ እንዳይጠናቀቅ እና የሚፈለገው ደረጃ ላይ እንዳይደረስ የሚከፈቱ ፕሮፖጋንዳዎች ላይ በዝርዝር ውይይት ተደርጎ ግልፅ አቅጣጫ መቀመጡንም አስታውቀዋል። ይሁን እንጂ ፣ በኤፍቢሲ ዘገባ ላይ ፣ ስለተቀመጠው አቅጣጫ በዝርዝር የተባለ ነገር የለም፡፡
ምርጫን በተመለከተም የ2013 ምርጫ ሰላማዊ፣ ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድም ሆነ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ እንዲሆን አቅጣጫ መቀመጡን አስታውቅዋል።
የብልጽግና ፓርቲ የሚጠበቅበትን ሁሉ አሟልቶ በዚህ ሂደት ውስጥ ለማለፍ ዝግጅት ማድረጉንም የፓርቲው ዋና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብናልፍ አንዷለም በመግለጫቸው አስታውቅዋል።