“በመጪው ምርጫ ተመጣጣኝ ውክልና ስርዓትን ለመተግበር እንቸገራለን” ብርቱካን ሚዴቅሳ
ተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ስርዓት ኢትዮጵያ እስካሁን ከምትከተለው የምርጫ ስርዓት በምን ይለያል?
ተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ስርዓት ለመጠቀም ጊዜ እንደሚጠይቅ ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ገልጸዋል
ተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ስርዓት ለመጠቀም ጊዜ እንደሚጠይቅ ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ገልጸዋል
በ2013 ዓ.ም ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀውን ምርጫ በተመለከተ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ውይይት አድርገዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎች በተገኙበት መድረክ ላይ ለምርጫ መጣደፍ አይገባም፤ ለምርጫ ምቹ ሁኔታ ይፈጠር፤ የሕግ የበላይነት ይከበር፤ የምርጫ ደንብ ይዘጋጅ፤ የፓርቲዎች ተሳታፊነት ይረጋገጥ የሚሉና ሌሎች ጉዳዮች ተነስተዋል፡፡
በዚሁ መርሃ ግብር ላይ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) በተለያዩ ሀገራት ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉ የብዙኃን ወይም አብላጫ ድምጽ ፣ የተመጣጣኝ ውክልና እና ቅይጥ የምርጫ ሥርዓቶችን አብራርተዋል፡፡
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚዴቅሳ በበኩላቸው ከቀረቡት አማራጮች መካከል በዚህ ዓመት በሚደረገው ምርጫ ተግባራዊ ለማድረግ በቦርዱ የታቀደውና ዝግጅት እየተደረገ ያለው የብዙኃን ወይም አብላጫ ድምጽ ውክልና መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከቀረቡት አማራጮች ውስጥ የተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት በተለያዩ አካላት ሲነሳ እንደነበር አንስተው ይህንኑ መነሻ በማድረግ ጥናት ተጠንቶ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ በዚህ ዓመት ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቀው ምርጫ የጊዜ ገደብ በመኖሩ ይህንን አዲስ የምርጫ ስርዓትን ለማሻሻል አስቸጋሪ እንደሚሆንም ተናግረዋል፡፡
ምንም እንኳን የትኛው የምርጫ ሥርዓት ይሻላል የሚለው የቦርዱ ስልጣን እንዳልሆነ ቢገልጹም ተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ አይነትን ተግባራዊ ማድረግ ካስፈለገ ግን የተዘጋጁ መመሪያዎችን ማሻሻል ይጠይቃል ነው ያሉት፡፡ ከዚህ ባለፈም ተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ ተጨማሪ ስልጠናዎችን መስጠት እና ሌሎችንም ሥራዎች እንደ አዲስ መሰራት ስለሚጠይቅ ግራ መጋባት ሊኖር ይችላል ብለዋል ሰብሳቢዋ፡፡ በቂ ጊዜ አለን ብለን አናምንም ያሉት ወ/ሪት ብርቱካን ጉዳዩን በተመለከተ ለመንግስት መግለጻቸውን ተናግረዋል፡፡
“በ2013 ምርጫ ተመጣጣኝ ውክል የምርጫ ሥርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ እንቸገራለን” ያሉት ወ/ሪት ብርቱካን ”የምርጫ ስርዓቱ የሚጠቅም ሊሆን ቢችልም ይህን ለመተግበር ትክክለኛ ጊዜ ነው ብለን አናምንም” ብለዋል፡፡ ተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ስርዓትን ተግባራዊ ብናደርግ ብዙ የተዘጋጀንባቸውን ነገሮች መልሶ መስራት ይጠይቃልም ነው ያሉት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በበኩላቸው የብዙኃን ወይም አብላጫ ድምጽ ውክልና 91 ሀገራት የሚጠቀሙበት መሆኑን ገልጸው ዋናው ጉዳይ ግን የምርጫ ስርዓት ሳይሆን የፖለቲካ ባህልና የመንግስት ቁርጠኝነት ነው ብለዋል፡፡
ተመጣጣኝ ውክል የምርጫ ስርዓትን ለመተግበር የሕገ መንግስት መሻሻልን እንደሚጠይቅ አንስተው ተጨማሪ ጊዜም እንደሚያስፈለግ ተናግረዋል፡፡ ይሁንና በዚህኛው ምርጫ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምክር ቤቶች የሚወከሉበት ሁኔታ ዝግ ከሆነ በሚቀጥለው የምርጫ ጊዜ ሕገ መንግስቱ ከተሻሻለ ዕድል እንደሚገኝ እና እስከዚያ ድረስ ግን መወያየትና መመካከር የተሸለ እንደሆነ አንስተዋል፡፡
የአብላጫ ድምጽ የምርጫ ስርዓት እስካሁን ኢትዮጵያ የምትከተለው የምርጫ ስርዓት ሲሆን በፓርቲ የተወከሉ አሊያም የግል እጩዎች ለፌዴራሉ የሕዝብ ተወካዮች ወይም ለክልል ም/ቤቶች የሚወዳደሩበት ነው፡፡ በዚህ የምርጫ ስርዓት አብላጫ ድምጽ ያገኘው እጩ አሸናፊ ሆኖ የምክር ቤት ወንበር ያገኛል፡፡
ተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ስርዓት በአንጻሩ የተለያየ አተገባበር ቢኖረውም ግለሰቦች ሳይሆኑ ፓርቲዎች የሚወዳደሩበት ሲሆን ድምጽ ሰጪዎች ለፓርቲዎች በሰጡት የድምጽ መጠን ልክ እያንዳንዱ ፓርቲ የተወዳደረበትን የምክር ቤት ወንበር ይከፋፈላል፡፡ ይህ የምርጫ ስርዓት የእያንዳንዱ መራጭ ድምጽ የተሻለ ዋጋ እንዲኖረው የሚያደርግ ሲሆን በርካታ ፓርቲዎችም ባገኙት የድምጽ ብዛት በምክር ቤት ውክልና እንዲኖራቸው ያስችላል፡፡ በሌላ በኩል ይህ የምርጫ ስርዓት አልፎ አልፎ አንድ ፓርቲ ብቻውን መንግስት ለመመስረት የሚያስችለውን ድምጽ እንዳያገኝ ያደርጋል፡፡ ይህም ፓርቲዎች መግባባት ከቻሉ በጥምረት መንግስት እንዲመሰርቱ አሊያም ድጋሚ ምርጫ እንዲካሔድ ሊያስገድድ ይችላል፡፡ ከዚህ አንጻር ተደጋጋሚ ፈተናዎች የሚገጥሟቸውን እስራኤልን እና ጣሊያንን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
ቅይጥ የምርጫ ስርዓት ደግሞ ከላይ የተገለጹት ሁለት የምርጫ አይነቶች በተለያየ መጠን ተግባራዊ የሚሆኑበት ነው፡፡
በኢትዮጵያ ሀገራዊ ለውጡ ከመከሰቱ በፊት ፣ የፈረሰውን ኢሕአዴግን ጨምሮ በርካታ ፓርቲዎች ቅይጥ የምርጫ ስርዓት እንዲተገበር ከስምምነት ላይ ደርሰው እንደነበር ይታወሳል፡፡