ከኢትዮ-ሱዳን የድንበር ግጭት በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከሱዳኑ መሪ አል ቡርሃን ጋር ተወያዩ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከሱዳኑ መሪ አልቡርሃን ጋር የመከሩት በኬንያ ነው
ሱዳን ወታደሮቼ በኢትዮጵያ ተገደሉብኝ ማለቷን ተከትሎ በሁለቱ ሀገራት መካከል ውጥረት ነግሶ ነበር
ከኢትዮጵያ እና ሱዳን የድንበር ግጭት በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከሱዳኑ መሪ ጄነራል አልቡርሃን ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ተገናኝተዋል።
የሱዳን ሉአላዊ የሽግግር መክር ቤት ቤት ሊቀመንበር አብዱልፈታህ አል ቡርሃን በኬንያ ዋና ከተማ በናይሮቢ ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዛሬ ተገናኝተዋል።
በቅርቡ በሁለቱ ሀገራት ድንበር ላይ ከፍተኛ ውጥረት ነግሶ ነበር።
የሱዳን ሉዓላዊነት ምክር ቤት በመግለጫው “አል-ቡርሃን እና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በኬንያ ርዕሰ መዲና ናይሮቢ ዝግ ስብሰባ እያደረጉ ነው” ሲል ተጨማሪ ዝርዝር መረጃን ሳይጠቅስ ገልጿል።
አል-ቡርሃን እና አብይ አህመድ በናይሮቢው ስብሰባ ላይ ተገኝተው በመተቃቀፍ እና በመጨባበጥ ፈገግታ ተለዋወጡ።
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የአሁኑ ስብሰባ በሱዳን የሚመራው አስቸኳይ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ዛሬ ማክሰኞ ማለዳ ላይ አል-ቡርሃን ናይሮቢ ገብቷል።
ባለፈው ሰኔ ወር መጨረሻ ላይ 7 የሱዳን ወታደሮች እና አንድ ዜጋ መገደላቸውን ተከትሎ በካርቱም እና በአዲስ አበባ መካከል አዲስ የድንበር ውጥረት ተፈጠረ።
የሱዳን መከላከያ ሚኒስቴር የሱዳን ወታደሮች በኢትዮጵያ ተገደሉ የሚል ክስ ከማቅረብ አልፎ እርምጃ እወስዳለሁ የሚል መግለጫ ሰጥቶ ነበር።
ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የሱዳን ወታደሮች የኢትዮጵያ ድንበር ጥሰው ትንኮሳ መፈጸማቸውን ገልጾ ነበር። የሱዳንን ክስ ያስተባበለው መንግስት በግድያው ማዘኑን መግለጹ ይታወሳል።
በመቀጠልም አል ቡርሀን ካርቱም ከጎረቤት "ኢትዮጵያ ጋር መደበኛ እና ሚዛናዊ ግንኙነት ትፈልጋለች" ማለታቸውን ተከትሎ ውጥረቱ የረገበ ይመስላል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም በወቅቱ ችግሮችን በሰላም መፍታት እና ጉርብትናን ማስቀደም ይገባል ብለው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ በኬንያ ከአል ቡርሃን ባደረጉት ውይይት ሁለቱ ሀገራት በትብብር ለመስራት በርካታ ጉዳይ መኖራቸውን እና ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ተስማምተናል ብለዋል።