የሱዳን ጦር አዛዥ ከኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ የሚገኘውን የሃገራቸውን ጦር ጎበኙ
ሱዳን፤ የኢትዮጵያ ጦር ሰባት ወታደሮቼንና ምርኮኞችን ገደለብኝ ስትል መክሰሷ ይታወሳል
ሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደሯን ወደ ካርቱም ጠርታለች
የሱዳን ጦር አዛዥ እና የሃገሪቱ ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበር ሌ/ጄ አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን ከኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ የሚገኘውን የሃገራቸውን ጦር ጎበኙ፡፡
ቡርሀን ትንሹ ፋሻጋ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኙት አል ዑስራ እና ዋድ ኮሊ አካባቢዎች የሚገኘውን የሃገራቸውን ጦር ነው ዛሬ ሰኞ ሰኔ 20 ቀን 2014 ዓ/ም የጎበኙት፡፡
ጉብኝቱ፤ ሱዳን "ወታደሮቼ ተገደሉብኝ" ማለቷን ተከትሎ የተካሄደ ነው፡፡ ካርቱም የኢትዮጵያ ጦር ሰባት ወታደሮችን እና ምርኮኞችን ገደለብኝ ስትል መክሰሷ ይታወሳል፡፡
"የአጸፋ ምላሽንማ ሳንሰጥ አንቀርም" ሲል ከተነበበው የሃገሪቱ ጦር መግለጫ በኋላ እምብዛም ሳይቆዩ ነው ቡርሃን ወደ አል ፋሽጋ የመጡት፡፡
በጉብኝታቸው ጦሩ የሃገሩን ዳር ድንበር ለመጠበቅ የሚያደርገውን ጥረት ለመደገፍ ቁርጠኛ ስለመሆናቸው ገልጸዋል፡፡ ለሃገራቸው ሲሉ መስዋዕትነትን የሚከፍሉ የጦሩ አባላት ደም "በከንቱ ፈስሶ" እንደማይቀርም ነው ቡርሃን የተናገሩት፡፡
ሁኔታው ተጨባጭ መልስ እንደሚያገኝ ቃል በመግባትም ከሰሞኑ በአል ዑስራ ያጋጠመው ፈጽሞ አይደገምም ብለዋል፡፡
በሱዳን መሬቶች ላይ የሚደረግ ምንም ዐይነት እንቅስቃሴ እንዳይኖር ሲሉም ቀጭን ትዕዛዝን አስተላልፈዋል፡፡
የአካባቢውን ማህበረሰብ የመሰረተ ልማትና ሌሎችንም ጥያቄዎች ለመመለስ እንደሚሰሩ ቃል ገብተውም ነው ቡርሃን ወደ ካርቱም የተመለሱት፡፡
አል ፋሽቃ፤ ኢትዮጵያ እና ሱዳን የባለቤትነት ጥያቄ የሚያነሱበት ሰፊና ለም መሬት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ጦርነት ላይ መሆኑን ተከትሎ ወደ አካባቢው ዘልቆ የገባው የሱዳን ጦር መሬቱን ይዞ ይገኛል፡፡ መሰረተ ልማቶችን ለመገንባትም ጥረት እየተደረገ ነው፡፡
ጦሩ መሰረተ ልማቶችን መገንባቱን አቁሞ ቀድሞ ወደ ነበረበት እንዲመለስ ደጋግማ የጠየቀችው ኢትዮጵያ ሃገራቱን የሚያወዛግቡ የድንበር ጉዳዮች በጋራ ኮሚቴው በኩል እንዲታዩ መጠየቋ ይታወሳል፡፡
"ሰባት ወታደሮቼ እና ምርኮኞች ተገደሉብኝ" ስትል ዛሬ የከሰሰችው ሱዳን ግን ድርጊቱ ያለ አጸፋ ምላሽ እንደማይቀር ነው ዛሬ ስታሳስብ የነበረው፤ በጦሩ በኩል ባወጣችው መግለጫ፡፡
አዲስ አበባ የሚገኙትን አምባሳደሯን መጥራቷንም ነው፤ ጉዳዩን ወደ ጸጥታው ምክር ቤት ልትወስደው እንደምትችልም የገለጸችው፤ ካርቱም ያስታወቀችው፡፡
ሱዳን ስም ከማጉደፍ ድርጊቷ እንድትታቀብ ያሳሰበችው ኢትዮጵያ በበኩሏ ወደ ድንበር ዘልቀው የገቡት ወታደሮች በሚሊሻዎች እንጂ በመከላከያ ሰራዊት አባላቷ እንዳልተገደሉ ገልጻለች፤ በግድያው ማዘኗን በመጠቆም፡፡
አቶ ደመቀ መኮንን በቅርቡ "በሱዳን የተወሰደው ግዛታችን በየትኛውም መመዘኛ ይመለሳል" ሲሉ ለተወካዮች ምክር ቤት መናገራቸው ይታወሳል፡፡